በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፓሊስና ማህበረሰብ በቅርበት በመስራታቸው የወንጀል ድርጊቶች በአንፃራዊነት እየቀነሰ መምጣቱ ተገለፀ
በከተማዋ የሚገኙ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የከተማው ፓሊስ ፅ/ቤት አስተውቋል።
የዎላይታ ሶዶ ከተማ ፓሊስ አመራሮች እና አባላት ባካሄዱት የጋራ መድረክ እንደ ተገለፀው ፓሊስና ማህበረሰቡ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በቅርበት በመስራታቸው የወንጀል ድርጊቶች በአንፃራዊነት መቀነሱን ተገልጿል።
መድረኩን የመሩት የከተማ ፓሊስ አዛዥ ሻለቃ ኡፋይሳ ቄልታ እንዳስታወቁት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ሰላምና መረጋጋት ህብረተሰቡ በቁርጠኝነት ሰላሙን በመጠበቁ እና የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት በመስራታቸው ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ሻለቃ ኡፋይሳ አክለውም ህብረተሰቡ አጠራጣሪ የሆኑ ጉዳዮችን ለፀጥታ አካላት በመጠቆም የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ከተማ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ዘገባ ወንጀል የእድገትና የልማት ፀር ነው ያሉት የከተማ ፓሊስ ዋና አዛዡ ከወቅታዊ የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እና የህግ ማስከበር ሂደቱ ጋር በተያያዘ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
