GridArt_20260904_181221120

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እሳት ቃጠሎን አስመልክቶ የተዘጋጀው ጥልቅ የምርመራ ዘገባ ከውድመት ዝርዝር ባለፈ የታቀዱ ሴራዎችንና የህዝብ ስጋቶችን በይፋ አጋልጠዋል።

​ትናንት በWT Media የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ማህበራዊ ሳይንስ ሕንፃ ላይ በደረሰው አውዳሚ የእሳት አደጋ የወደሙትን ንብረቶች ዝርዝር በይፋ ማሳወቃችን ይታወሳል።

እስከ 140 ኮምፒተሮች የሞሉባቸው ሁለት ትልልቅ የአይሲቲ ላብራቶሪዎች፣ የ7 ኮሌጆች የፋይናንስና የሰው ሀብት ቢሮዎች፣ የሬጅስትራር መዝገቦች፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እና የጂኦግራፊ ጂፒኤስ ላብራቶሪዎች እንዲሁም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግመት ያላቸው ንብረቶች መውደማቸውን በአንባብያን ዘንድ አድርሰናል።

​ይሁን እንጂ ጉዳዩን እንደ ተለመደ “ድንገተኛ የእሳት አደጋ” ብቻ አድርጎ ማለፍ ፈጽሞ የማይታሰብ እና ከእውነታው የራቀ ነው። ትናንት የቀረበውን የጉድለት ዝርዝር መሰረት በማድረግ ከዚህ አውዳሚ ክስተት ጀርባ ያሉ ጥልቅና አሳሳቢ የፖለቲካ እና የሴራ እውነታዎች የሚከተሉትን ቁም ነገሮች ያሳያሉ።

​አደጋው ከመከሰቱ ከሶስት ቀናት በፊት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የነበረው ብቸኛ የእሳት ማጥፊያ መኪና “ለጥገና” በሚል ሰበብ ከከተማው ውጪ እንዲወጣ መደረጉ እንዲሁም የእሳት አደጋው አብዛኛው ሰራተኛ ለምሳ በወጣበት ሰዓት መሆኑ ጉዳዩ ድንገተኛ አደጋ ሳይሆን ሆን ተብሎ ተቋም ለማጥፋት የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑን ያጋልጣል ሲሉ የአከባቢው ነዋሪዎች ይገልፃሉ።

እሳት አደጋ በየጊዜው በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለበት ከተማ የራሷ የእሳት ማጥፊያ መኪና እንኳን እንዳይኖራት ማድረግ፣ እርዳታ ከርቀት ከአርባምንጭና ከሽንሽቾ እንዲጠራ መደረጉ የከፋ ቸልተኝነት እና ሆን ተብሎ ተቋማት እንዲወደሙ የተደረገ ግልጽ ወንጀል ነው” በሚል በርካቶች ሀሳባቸውን እየገለፁ ነው።
​
​”ለአካባቢው ገጽታ ጥሩ አይደለም” በሚል አሳባዊ ምክንያት የዎላይታ ካድሬዎች በዩኒቨርሲቲው የደረሰውን ግዙፍ ውድመት እንዳይነገር ጥብቅ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

አደጋው “በቁጥጥር ስር ውሏል” የሚል የይስሙላ ዜና ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ከማሰራጨት ውጪ፣ አንድም ኃላፊነት ያለው አመራር በወቅታዊው አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ግልጽ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። አጀንዳውን ለማስቀየስም በካድሬ-ቅብ ግለሰቦች አማካኝነት የተዛቡ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩ እንደሚገኙ WT Media ለመታዘብ ችሏል።

​ከእሳት አደጋ ባሻገር በሕዝብ ላይ የተቃጡ ተደጋጋሚ ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተመለከተ ​ምሁሩና የዎላይታ ሀዝብ ተወካይ ዶ/ር ተሾመ ታከለ እንዳሉት «ከእሳት አደጋ ባሻገር በሕዝባችን ላይ የተቃጣ ተደጋጋሚ ሰው ሰራሽ አደጋ ነው። በሀገራችን ከአዲስ አበባ መርካቶ ቀጥሎ በደቡብ ኢትዮጵያ ታላቁ የዎላይታ ሶዶ መርካቶ ገበያ በድንገተኛ የእሳት አደጋ ዶግ አመድ ሆኗል፤ አንጋፋው ኦቶና ሆስፒታልም እንዲሁ ውድሟል፤ ዛሬ ደግሞ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ላይ አደጋ ተደቅኗል»።

“በዓለም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በየጊዜው በአንድ ከተማ ብቻ “ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት” በተመሳሳይ ሁኔታ እየወደሙ መሄዳቸው በቀጣይ እንደ ሕዝብ ሊበላን የሚችል አደገኛ እሳት መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል” ብለዋል።

“​መዋቅር ጠይቀን ተገደልን፣ ልማት ጠይቀን የነበረውም እንዲወድም እየተደረገ ነው፤ ለወጣቶች ስራ ሲጠየቅ መፍትሔ አጥተው በተሰደበትም ወደ ጦርነት እንዲገቡ እያፈሱ ነው! ህዝብ ተጨማሪ ልማት ሲጠይቅ እነሱ በየጊዜው እያዘናጉ የነበረውን እያወደሙ ነው” የሚለውም የአከባቢው ህዝብ ትልቅ ቅሬታ ሆኗል።

“​በየጊዜው በአካባቢው በሚገኙ ትላልቅ ተቋማት ውድመት ዙሪያ አስቸኳይ ጥልቅ ምርመራ ተደርጎ ምክንያቱ መታወቅ አለበት። ህዝባዊ መድረክ ተካሂዶ ዘላቂ መፍትሔ ካልተቀመጠ፣ ነገም ሌላውን የማውደሙ ዘመቻ መቀጠሉ አይቀርም” የሚል ሀሳብ በርካቶች የሚስማሙበት ነው።

​🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፥ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media