“ማንነታቸውን ስለጠየቁ ብቻ በቁጫ ህዝብ ላይ ከሰማይ በታች ያለው ሁሉ በደልና ሰብዓዊ መብት ጥሰት በጋሞ አመራሮች እየደረሰ ነው” ሲል ቁሕዴፓ ከሰሰ​

​በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና የሰላማዊ ትግል ምህዳር ላይ ከባድ ጥያቄዎችን የሚያስነሳው የሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ መጠናቀቅን እና ሀገራዊ የምክክር ሂደቶችን ተከትሎ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) ለWT Media ባደረሰው ይፋዊ መግለጫ በቁጫ መዋቅሮች ውስጥ ተባብሰው የቀጠሉ አሰቃቂ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን አጋልጧል።

​WT Media ከዚህ ቀደምም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቁጫ፣ በዘይሴ እና በሌሎችም አጎራባች ማህበረሰቦች ላይ በምርጫ ወቅት የተፈጸሙ የተደራጁ የኃይል ጥቃቶች፣ የጅምላ እስራቶች፣ የፓርቲ ጽህፈት ቤቶች ውድመት፣ የአባላት መታወቂያዎች በአደባባይ መቃጠል፣ እንዲሁም የዜጎችን መሰረታዊ ነፃነት የማፈን ዘመቻዎች በተደጋጋሚ ሲዘግብ ቆይቷል።

​በወቅቱ የመንግስት አካላት እና የጸጥታ መዋቅሮች በዝምታ ያለፉዋቸው ወይም በግልጽ የደገፏቸው እነዚህ መዋቅራዊ በደሎች፣ አሁን ላይ የሀገሪቱን የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምህዳር ከዜሮ በታች አውርደውት የቆዩ ቢሆንም፤ ችግሩ አሁን ላይ ይበልጥ ተባብሶ በዜጎች መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ላይ ቀጥተኛ አደጋ እየጣለ ይገኛል።

​ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ፍትሕ እና እኩልነት ለማረጋገጥ ታሪካዊ የምክክር ሂደቶችን ባደረገችበት ወቅትም ጭምር፣ በቁጫ ሦስቱ መዋቅሮች (ቁጫ ወረዳ፣ ቁጫ አልፋ ወረዳ እና ሰላምበር ከተማ አስተዳደር) ውስጥ ከሕግ ውጭ የሆኑ ድርጊቶች ያለከልካይ እየተፈጸሙ ይገኛሉ ሲል ቁሕዴፓ ባወጣው በመግለጫው ገልጿል።

እንደ ፓርቲው መግለጫ ​ለአርባ ምንጭ ስቴዲየም እና ለጋሞ መስቀል በሚል ስም ዜጎች አቅማቸውን በሚያልፍ መጠን ገንዘብ እንዲከፍሉ በግድ መገደዳቸው ተረጋግጧል። የክፍያ ደረሰኝ ሳይሰጥ ገንዘብ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ ለመክፈል አቅም የሌላቸው ወይም ይህንን አሰራር የተቃወሙ ዜጎች ታስረው እንዲደበደቡ ተደርጓል።

 ልማት በግዴታ፣ በማስፈራራት እና በኃይል ሊሠራ እንደማይችል የሚገልጸው ፓርቲው፣ ዘላቂ ልማት የሚገነባው በሕዝብ ተሳትፎ እና በግልጽነት እንጂ በግፍ ሊሆን እንደማይገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

​ዜጎች ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ እና ያለ ሕጋዊ ሂደት መታሰራቸው እና መደበደባቸው የሰውን የአካል ደህንነት እና ነፃነት በቀጥታ የሚጥስ ወንጀል መሆኑ ተገልጿል። የፖለቲካ ልዩነት ወንጀል እንዳልሆነ እና የፓርቲ አባልነት ለእስር ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ ቢታወቅም፣ በቁጫ መዋቅሮች ውስጥ የፓርቲ አባላት ሁለቱ ሆኖ በሻይ ቤት መቀመጥ ወይም ማህበራዊ መድረኮችን መካፈል እንዳይችሉ አፈናው ከዜሮ በታች ወርዷል።

​በቁጫ ወረዳ ዳሆ፣ ሰላምበር ከተማ እና ዳና ቀበሌን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የሕዝብና የመንግሥት መሬት በኢንቨስትመንት ስም በሕገ-ወጥ መንገድ ተዘርፏል። 

መሬት የሕዝብ የኑሮ መሠረት በመሆኑ ያለ ሕጋዊ ሂደት መወሰዱ አግባብ አይደለም። በተለይም በዳና ቀበሌ በግብርና ኢንቨስትመንት ስም ተወስዶ የነበረው መሬት ወደ ማዕድን ሀብት ብዝበዛ መቀየሩ፣ ለአንድ ዓላማ የተሰጠ ፈቃድ ሕዝብን ለመንጠቅና ሙስናን ለማንገስ እየዋለ መሆኑን ያሳያል ብሏል ፓርቲው።

​በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የበልግ እና የመኸር ምርት ቀንሶ በቁጫና ቁጫ አልፋ ወረዳዎች ድርቅ መከሰቱ ተመላክቷል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሕዝቡ ከዝርፊያ ይልቅ ድጋፍና ጥበቃ የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ መዋቅሮቹ የሚሰጡት ምላሽ ግን እስር፣ ድብደባ እና የገንዘብ መቀጮ ሆኗል። አዛውንቶች ጭምር ከቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ስቃይ ተጋልጠዋል።

​ማንኛውም ዜጋ በማንነቱ ወይም በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት መታሰር የለበትም የሚለው ቁሕዴፓ፤ በቁጫ ውስጥ የተፈጸሙት ሕገ-ወጥ እስሮች፣ የገንዘብ መዋጮዎች፣ የመሬት ቅርምቶች እና የተፈጥሮ ሀብት ዝርፊያዎች ወዲያውኑ እንዲቆሙ ጠይቋል።

​WT Media ቀደም ሲል እንደዘገበው ሁሉ የዜጎችን ሰብአዊ መብትና ደህንነት ማረጋገጥ ያልቻለ የዴሞክራሲ ሂደት ትርጉም አልባ ስለሚሆን፤ የፌዴራል መንግስት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ህግ አክባሪ አካላት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጡና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሰጠውን አጠቃላይ መረጃ ለታሪክና ለህዝብ ማድረጉን ይቀጥላል።

የጥሰቶቹ ተዋናይ የሆኑ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እና ለተጎዱ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግ አጥብቆ ይጠይቃል።

በጋሞ ዞን ውስጥ በቁጫ እና በዘይሴ ብሔረሰቦች ላይ የተከፈተው ይህ ጥቃት በምርጫ ወቅት ካሳዩት የፖለቲካ አቋም እና ካነሱት የማንነት ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ሁለቱም ወገኖች ያረጋግጣሉ።

ቁሕዴፓ በመግለጫው የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና ተቆርቋሪ ወገኖች የፌዴራል መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂዱ በጽኑ እየጠየቁ ይገኛሉ።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media