1000144391

ባለፉት ቀናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ አዋሳኝ ዞኖች እና ወረዳዎች በተቀሰቀሱ አጥፊ ግጭቶች በንጹሃን ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

​ግጭቱ የፈነዳው 21 የሚሆኑ የበና ፀማይ ከብቶች በባለታወቁ ሰዎች መወሰዳቸውን ተከትሎ “ዘራፊዎቹ ወደ ኮልሜ አቅጣጫ ተጓዙ” የሚል ሀሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ነው። ማንነታቸውና ከብቱ በግልጽ የት እንደተወሰደ ሳይረጋገጥ፣ ከኧሌና ከደቡብ ኦሞ ዞን አስቀድመው ለጥቃት የተዘጋጁ ታጣቂዎች በተቀናጀ ሁኔታ ጥቃት ከፍተዋል።

በዚህም በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ ኩርቦ እና ማሶያ ቀበሌዎች ውስጥ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 5 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 4 ቆስለዋል፤ ቁስለኞቹ በካራት ሆስፒታል እየታከሙ ይገኛሉ። ጥቃት አድራሾቹ የመኖሪያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና የጤና ኬላዎችን በእሳት ማቃጠላቸውን የዓይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

​በወቅቱ በደረሰው አጠቃላይ ጥቃት ህፃናትንና አረጋውያንን ጨምሮ ከ7 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ከቀናት በፊት በ WT Media የተጠናቀረው መረጃ ያመለክታል።

አካባቢውን ከጥቃት ለመከላከል ተሰማርተው የነበሩ የክልሉ አድማ ብተና እና የፌዴራል ፖሊስ ኃይሎች በድንገት ከስፍራው እንዲወጡ መደረጋቸው ለጥቃቱ መባባስ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል። የኮንሶ እና የኧሌ ዞን አመራሮች ግጭቱን ለማስቆም አቅደው የነበረ ቢሆንም ከኧሌ አመራሮች በኩል ወደ ስፍራው ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ዕቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል።

​በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሃንስ ጋሹ “በእኛ ማህበረሰብ እንዲህ አይነት ድርጊት አልፈጸመም፤ ነገር ግን ጣልቃ የገቡ አካላት አሉ፤ ከዚህ በፊት ተፈናቅለው ወደ ወረዳው ከገቡ የአሌ ማህበረሰብ መካከል አንዳንዶቹ ጉዳዩን በዋናነት ያስተባበሩበት ሁኔታ አለ” ብለዋል።

በተመሳሳይ የአሌ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አሊፋ ራኪሌ ከኮንሶ ዞን ጋር በሚዋሰኑ አጎራባች ቀበሌዎች ውስጥ መጠቃቃቶች መፈጸማቸውን አረጋግጠው፣ ቅድሚያ አካባቢውን በማረጋጋት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

​በሌላ በኩል ዛሬ በ WT Media በተሰበሰበው አዲስ መረጃ መሰረት በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ በብልብላይታ ቀጠና ከጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል፤ እስካሁን በመንግስት በኩል የተደረገላቸው አንዳችም ሰብአዊ እርዳታ አለመኖሩን ነዋሪዎች አረጋግጦልናል።

በዚሁ በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ ኩርቦ ቀበሌ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከ385 በላይ አባወራዎች እና እማወራዎችን ጨምሮ ከ2,300 በላይ የቤተሰብ አባላት የሆኑ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አንድ የወረዳው አመራር ያረጋገጥልን ሲሆን ግጭቱ የሰብዓዊ ቀውስ ከመፍጠሩም በላይ የማህበረሰቡን መሰረተ ልማቶችና ተቋማት ውድመት አስከትሏል።

ግጭቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ተብሎ የሚታመነው የኮንሶ እና የኧሌ ወሰን ማካለል አለመግባባት ለረጅም ዓመታት የቆየ መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ጉዳዩ ከኮንሶና ከኧሌ ባለፈ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የሄደው በኮሬ ዞን ጭምር ነው። በኮሬ ዞን ጎልቤ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቦኮሶ በሚባል አካባቢ ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በኩል ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት ንጹሃን ወጣቶች ሕይወታቸው ማለፉን WT Media ከአከባቢው ምንጭ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ሳምንት ብቻ ከዞኑ 4 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውና በርካታ ከብቶች በዝርፊያ መወሰዳቸው ታውቋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት የክልሉ መንግስት በየጊዜው እየተፈፀመ ላለው ለንጹሃን ዜጎች ዕለታዊ መገደል እና መፈናቀል ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ ዝምታን መምረጡ ከፍተኛ አቤቱታ አስነሳቷል።

​ይሁን እንጂ ዛሬ መስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መኖሩን ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በፄማይ፣ ኮልሜና ኧሌ አካባቢ ተስተጉሎ የነበረው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አሁን ላይ ማለፍ መጀመሩ ተረጋግጧል።

WT Media ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ መረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፤ ሚዲያችን የጉዳዩን ሂደት በቅርበት እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።

​Voice of Marginalized Community – WT Media