GridArt_20260916_221004085

​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ አዋሳኝ ዞኖች እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ መደፍረስና የንጹሃን ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በኮንሶ፣ በኧሌ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች ከተከሰቱት መዋቅራዊና የወሰን ግጭቶች ጎን ለጎን፣ በኮሬ ዞን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ድንበር አካባቢ የተፈጠረው የጸጥታ መታወክ እና የኃላፊዎች የቃላት ጦርነት አዲስ አቅጣጫ ይዞል።

​በትናንትናው ዕለት WT Media በሰበሰበው መረጃ መሠረት እንደዘገበው ጉዳዩ ከኮንሶና ከኧሌ ውጥረት ባለፈ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የሄደው በኮሬ ዞን ጭምር ነው።

በኮሬ ዞን ጎልቤ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቦኮሶ በሚባል አካባቢ ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በኩል ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት ንጹሃን ወጣቶች ሕይወታቸው አልፏል።

በዚህ ሳምንት ብቻ ከዞኑ 4 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውና በርካታ ከብቶች በዝርፊያ መወሰዳቸው ተረጋግጧል።

​ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩን አስመልክቶ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሚዲያ ባወጣው ዘገባ፤ በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ ጎልቤ ቀበሌ በሞተር ሳይክል ወደ ኬሌ ከተማ ሲጓዙ የነብሩ ሁለት ሰላማዊ ወጣቶች ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ በታጣቂዎች በጥይት መገደላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች “መንግስት ባለበት ሀገር በፓርላማ ቢጮህም የሚሰማን አልተገኘም፤ የታጠቀው ሃይል በፈለገው ጊዜ ይገድለናል” ሲሉ ከፍተኛ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

​በወቅቱ የኮሬ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሲዲሞ ማዳሞ ጥቃቱን ማረጋገጣቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ የምዕራብ ጉጂ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ዳምባ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ አካባቢው “ኦነግ ሸኔ” እንቅስቃሴ የሚያደርግበት በመሆኑ ታጣቂው ቡድን ኮሬን እንደ ሎጅስቲክስ ምንጭ በመጠቀም ጥቃት እንደሚፈጽም ገልጸው ነበር።

ይህ መግለጫ በኮሬ ዞን በኩል ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

​የምዕራብ ጉጂ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ለቲክቫህ ሚዲያ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም መስከረም 6 ቀን 2019 ዓ/ም የኮሬ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ይፋዊ መግለጫ አውጥቷል።

​በመግለጫውም ​የተሳሳተ ውንጀላ እንዲታረም ጥሪ አቅርቧል።

የምዕራብ ጉጂ ዞን ኃላፊ “የኮሬ ዞን ነዋሪዎች ለሸኔዎች የሎጅስቲክስ ምንጭ ሆነው እያገለገሉ ነው” የሚለው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ከእውነታ የራቀ፣ የራሳቸውን የጸጥታ መዋቅር ክፍተት ለመሸፈን የተደረገ እና የኮሬን ሕዝብ ከሽብርተኛው ቡድን ጋር ለማያያዝ የታለመ አደገኛ ሙከራ መሆኑ ተገልጿል።

​አክሎም የኮሬና የጉጂ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በጋብቻና በማህበራዊ ቁርኝት የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች መሆናቸውን በመግለጽ አሁን ያለው ችግር የጸረ-ሰላም ሃይሎች አጀንዳ መሆኑን አመላክቷል።

​መግለጫው የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል መዋቅር ይህንን ቀውስ ተራ የድንበር ግጭት ሳይሆን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ አድርገው በመረዳት አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል ሲል አሳስቧል።
​
​በአካባቢው በተፈጠረው ውጥረትና የሰብአዊ ቀውስ ሳቢያ ንጹሃን ዜጎች ለከፍተኛ ስጋትና መፈናቀል የተጋለጡ ሲሆን ሚዲያዎችና የመንግስት አካላት ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድ በመከተል ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጁ ነዋሪዎች በአጽንኦት እየጠየቁ ይገኛሉ።

WT Media የጭቁኖችና የሰላም ፈላጊዎች ድምፅ በመሆን በደቡብ ኢትዮጵያ አዋሳኝ ዞኖች እየተከሰቱ ያሉትን መዋቅራዊ ችግሮችና የጸጥታ ቀውሶች በቅርበት እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።

​ Voice of Marginalized Community – WT Media