“ከጥንት ጀምሮ ስናከብር የመጣነው የራሳችን ዘመን መለወጫ እያለን “ዮ ማስቃላ” የተባለውን ሀይማኖታዊ በዓል እንድናከብር እየተገደድን ነው” ሲሉም የቁጫ እና የዘይሴ ብሄረሰቦች ቅሬታ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የህዝቦችን ባህል፣ ታሪክ እና የዘመን አቆጣጠር እሴቶች በነፃነት የማስጠበቅና የማሳደግ መብት በህገ-መንግስታዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተረጋገጠ ቢሆንም፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ግን ከዚህ በተቃራኒው የባህልና የማንነት ቀውስ እየተከሰተ መሆኑ ተሰምቷል።
የዘይሴ እና የቁጫ ብሔረሰብ ተወካዮች ለ WT Media በሰጡት ጥልቅ መረጃ የዞኑ እና የክልሉ አስተዳደር አካላት የህዝቡን እውነተኛ የዘመን መለወጫ በግድ በመሻር ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን በዓላት በኃይል እንዲያከብሩ እያስገደዷቸው መሆኑን በብርቱ አጋልጠዋል።
WT Media ከዚህ ቀደም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቁጫ፣ በዘይሴ እና በሌሎችም ማህበረሰቦች ላይ የሚፈጸሙትን ስልታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የፓርቲ ጽህፈት ቤቶች ውድመት፣ የአባላት መታወቂያዎች በአደባባይ መቃጠል፣ እንዲሁም የዜጎችን መሰረታዊ ነፃነት የማፈን ዘመቻዎች በተደጋጋሚ ሲዘግብ ቆይቷል።
አሁን ላይ በዘይሴና በቁጫ ማህበረሰቦች ላይ እየተካሄደ ያለው የባህልና የማንነት ስረዛ ዘመቻም ከዚህ ቀደም ከነበሩት መዋቅራዊ በደሎች እና ፖለቲካዊ አፈናዎች ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑ ተረጋግጧል።
የዛይሴ ብሔረሰብ ላለፉት አስራ ስድስት ክፍለ ዘመናት ሉአላዊ ግዛቱን አስጠብቆ የኖረ፣ ከሃያ በላይ ነገሥታት ተፈራርቀው ያስተዳደሩት እና የቱባ ባህል ባለቤት የሆነ ኩሩ ህዝብ ነው። በብሔረሰቡ የዘመን ቀመር መሰረት እውነተኛው የዘመን መለወጫ በዓል የሚከበረው በ’ቢዛ አጉና ቆስ ቢዞ’ (ሰኔ ወር የመጀመሪያ ቀን) ሲሆን፣ በብሔረሰቡ ቋንቋ “የዋ ሱሩቄ” በመባል ይታወቃልና በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

ይህ የዘመን አቆጣጠር ትክክለኛነት በ10ኛ ክፍል የዘይሴኛ አፍ መፍቻ ቋንቋ መጻሕፍት ላይ ጭምር ሰፍሮ ትውልዱ እየተማረበት የሚገኝ ታሪካዊ እውነታ ነው። ሆኖም የጋሞ ዞን እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ይህንን ሀቅ ቸል በማለት፣ ህዝቡ በግድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መስቀል በዓል የሆነውን እና በብሔረሰቡ ቋንቋ “ቡዶ ኬሶ” (ዳመራ) እየተባለ እንዲከበር የሚደረገውን አስገዳጅ ሁኔታ በፅኑ አውግዘዋል።

የዛይሴ ብሔረሰብ ላለፉት አስራ ስድስት ክፍለ ዘመናት ሉአላዊ ግዛቱን አስጠብቆ የኖረ፣ ከሃያ በላይ ነገሥታት ተፈራርቀው ያስተዳደሩት እና የቱባ ባህል ባለቤት የሆነ ህዝብ ነው። በብሔረሰቡ የዘመን ቀመር መሰረት እውነተኛው የዘመን መለወጫ በዓል የሚከበረው በ’ቢዛ አጉና ቆስ ቢዞ’ (ሰኔ ወር የመጀመሪያ ቀን) ሲሆን፣ በብሔረሰቡ ቋንቋ “የዋ ሱሩቄ” በመባል ይታወቃልና በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

ይህ የዘመን አቆጣጠር ትክክለኛነት በ10ኛ ክፍል የዘይሴኛ አፍ መፍቻ ቋንቋ መጻሕፍት ላይ ጭምር ሰፍሮ ትውልዱ እየተማረበት የሚገኝ ታሪካዊ እውነታ ነው። ይባስ ብሎም የዘይሴ ብሔረሰብ ማንነት በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክርቤት ጭምር በይፋ የተመዘገበ እና እውቅና የተሰጠው ነው።
ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ “የጋሞ ተወላጅ የሆነው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደ ለጋሞ ዞን አመራሮች በሰጡት ተልዕኮ መሰረት ህዝቡ ያልተቀበለውን እና የባህሉ አካል ያልሆነውን በዓል በኃይል ለማስፈጸም ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

በዚህም ምክንያት “የዘይሴ እና የቁጫ ብሔረሰብ አባላት የራሳቸው የዘመን መለወጫ (“የዋ ሱሩቄ” እና “ዎዳላ ጋዜ”) እያላቸው፣ “ዮ ማስቃላ” ወይም “ቡዶ ኬሶ” የተባለውን በዓል እንድታከብሩ ተገዳችኋል በሚል በፀጥታ ኃይሎች መፈራራቶች እየደረሱባቸው ይገኛል” በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።
ህዝቡ በድርቅ እና በከፋ የኑሮ ጫና ውስጥ ባለበት ወቅት፣ ከፍላጎቱ ውጭ የገንዘብ መዋጮዎች እንዲያዋጡ በግድ እየተጠየቁ ይገኛሉ።
አመራሩ ለጠባብ የፖለቲካ ፍጆታ ሲል የብሔረሰቡን ታሪክና ማንነት ለማደብዘዝ እና በፈጠራ ትርክት ለመተካት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለፅ ላለፉት ሦስት ዓመታት ይህንን አሰራር በኃይል ለማስፈጸም በተደረገው ሙከራ በርካታ ንጹሐን ዜጎች መገደላቸውን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በቁጫዎች የሚከበረውና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የቁጫ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል “ዎዳላ ጋዜ” (Wodala Gazze) እንጂ “ዮ ጋሞ ማስቃላ” አይደለም። የቁጫ ብሔረሰብ ከኦሞዓዊ ቋንቋ ቤተሰብ የሚመደብ፣ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር እና የጥንት ባህላዊ እሴቶች ያሉት ህዝብ ነው።

የቁጫ ሕዝብ ከጋሞ ሕዝብ ጋር የቆየ ማህበራዊ ትስስር ያለው ቢሆንም የብሔረሰቡን ስም እና ባህል ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ደባልቆ የማጥፋት ሰፊ ስልታዊ እቅድ በዞኑ መዋቅር እየተተገበረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
የቁጫ ሕዝብ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ላላችሁ ሁሉ «ቅርስ ያለው ታሪክ አለው» በሚል መርህ መሠረት የቁጫን ሕዝብ ታሪክና ባህል አካል የሆነውን “ዎዳላ ጋዜ” በዓልን በዩኔስኮ (UNESCO) ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የበኩላችሁን እንድትወጡ ጥሪ ቀርቧል።

የቁጫ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህል እና የዘመን አቆጣጠር ያለው ከኦሞዓዊ ቋንቋ ቤተሰብ የሚመደብ ኩሩ ህዝብ ነው። ይሁን እንጂ፣ ይህ ህዝብ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በጋሞ ዞን ውስጥ ተካቶ በመዋቅሩ ውስጥ ማንነቱ እንደተጨፈለቀበትና እንዳልተከበረለት ተወካዮቹ ይገልጻሉ።
የቁጫ ሕዝብ ከጋሞ ዞን አስተዳደር ነፃ ወጥቶ የራሱ የሆነ ልዩ መዋቅር እንዲሰጠው እና ማንነቱ በይፋ ታውቆ በራሱ አስተዳደር እንዲመራ ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ የቆየ ቢሆንም፣ እስካሁን አወንታዊ ምላሽ አላገኘም። ይህ ህገ-ወጥ አሰራር የህዝቡን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚጋፋና ፖለቲካዊ አፈናን ያዘለ መሆኑ ተመላክቷል።
WT Media ቀደም ሲል በቁጫ እና በዘይሴ ማህበረሰቦች ላይ የተፈጸሙትን የኃይል ጥቃቶች፣ የጅምላ እስራቶች እና መዋቅራዊ በደሎች በምርምርና በመረጃ አስደግፎ እንደዘገበው ሁሉ፤ አሁን ላይ በባህልና በማንነት ላይ እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ጫና በዝምታ እንደማያልፈው ያስታውሳል።
እንደ ብሄረሰቦች አባላት አስተያየት የዜጎችን ሰብአዊ መብት፣ ነፃነት እና የባህል ባለቤትነት ማክበር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሠረት ነው፤ የታሪክ እና የባህል ባለቤት መሆን ማለት ማንነትን በነፃነት ማሳደግ እንጂ ሃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን በጉልበት በህዝብ ላይ መጫን አይደለም።
ህዝቡ በልማት ኢፍትሃዊነት፣ በአየር ንብረት መዛባትና በድርቅ የተነሳ በከፋ የኑሮ ውድነት እና የድጋፍ እጦት መከራውን በማየት ላይ ባለበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከፍላጎቱ ውጭ የራሳቸውን ትተው ሃይማኖታዊ በዓላትን በጉልበት እንዲያከብር መገደዱ፣ በግዴታ ገንዘብ እንዲያዋጣ መደረጉ እና የፀጥታ ኃይሎች ሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ ድርጊቶችን መፈጸማቸው ተቀባይነት የሌለው አደገኛ አካሄድ ነውም ብለዋል።
በጋሞ ዞን አስተዳደር አካላት እና በጸጥታ መዋቅሮች እየተወሰዱ ያሉ ህገ-ወጥ እርምጃዎች እና የባህል ጫናዎች፣ በቁጫ እና በዘይሴ ማህበረሰቦች ላይ ከባድ፣ ስልታዊ እና አንገብጋቢ ሰብዓዊ ቀውስ እየፈጠሩ ይገኛሉ።
በመሆኑም የፌዴራል መንግስት፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት በዘይሴና በቁጫ ማህበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ህገ-ወጥ ጫና እና የማንነት ስረዛ ዘመቻ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጡበት አጥብቆ በመጠየቅ፤ የጥሰቶቹ አድራሾች በሕግ እንዲጠየቁ እና ለተጎዱ ዜጎች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርቧል።
Voice of Marginalized Community – WT Media