የዶክተር ዐቢይ አህመድ አገዛዝን “ለማስወገድ” የደቡብ ኢትዮጵያ ኃይሎች ያልተካተተበት የ7 ኃይሎች ጥምረት “የሕዝቦችን ህልውና ለመታደግ የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን” በሚል ተመስርቷል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን ሥርዓት አስወግደን “አካታች የሽግግር መንግስት” እንመሰርታለን የሚሉ ሰባት ኃይሎች ትብብር መመሥረቱ በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።
“የኢትዮጵያ ህዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለህልውና” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ይህን ጥምረት ከመሰረቱት መካከል የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ የኦጋዴን ህዝብ ነጻነት ግንባር፣ የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር፣ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ እና የጉሙዝ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የዚህ ኅብረት አባል መሆናቸው በመግለጫው ተመላክቷል።
መግለጫውን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን አማጺ ቡድን አፋብንን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ዘመነ ካሴ ያቀረቡት ሲሆን ጥምረቱ “የሕዝቦችን ህልውና መታደግ” እና “አካታች የሽግግር መንግስት መመስረት” የሚሉ አጀንዳዎችን ይዞ መነሳቱን አሳውቋል።

ይሁን እንጂ ይህ አዲስ የተቋቋመው ጥምረት ከጅምሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካዊ አቋም የፈጸመው ግልጽ ማርጅናላይዜሽን (Marginization) እንዲሁም ሆን ብሎ አካባቢውን አንደርማይን (Underestimate) የማድረግ አካሄዱ እጅግ አደገኛ እና አከራካሪ መሆኑ በሰፊው እየተተቸ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ በታሪክም ሆነ በወቅታዊው የሀገሪቱ የፖለቲካ ውጣ ውረድ ውስጥ ሁልጊዜም እየተገለለ፣ ድምጹ እየታፈነ እና ውሳኔዎች ላይ እንዳይሳተፍ እየተደረገ የኖረ ሕዝብ መሆኑ ይታወቃል።
አሁን ላይ የተቋቋመው ይህ ትብብር ከደቡብ ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ በመተው እና የአከባቢውን ህዝብ ሚና ፍጹም ኢንቫሊድ (Invalid) በማድረግ የጀመረው ጉዞ፣ ከቀድሞው ስርዓት የተረከበው የገለልተኝነት እና የማግለል በሽታ አሁንም መቀጠሉን በግልጽ ያሳያል።
በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጡ የደቡብ ኢትዮጵያ ምሁራንና አንጋፋ ፖለቲከኞች በጉዳዩ ዙሪያ ለ WT Media አሁን የተፈጠረውን አካሄድ አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል።
“የደቡብ ሕዝብ በታሪክም ሆነ በወቅታዊው ፖለቲካ ሆን ተብሎ እንዲገለል እየተደረገ ነው። አሁን አዲስ ጥምረት ፈጠርን የሚሉት አካላትም ከቀድሞዎቹ ገዥዎች ምንም የተለየ አካሄድ ሳይዙ፣ የደቡብ ኢትዮጵያን ሕዝብ ትልቅነት፣ ፖለቲካዊ ተሰሚነት እና ሚና ሙሉ በሙሉ አንደርማይን አድርገውና አጥፍተው ነው ወደዚህ የገቡት።”
“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነትና የሰላም እጦት ውስጥ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግስት ጎን ተሰልፎ፣ ለሀገር ህልውና ሲሉ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ፣ ደማቸውን እያፈሰሱ እና ህይወታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ መንግስት ለዚህ ሁሉ መስዋዕትነት እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ የልማት፣ የሰላም እና የፍትህ ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ ፍጹም አጥጋቢ አይደለም፤ በርካታ የልማትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች አሁንም መልስ አላገኙም።”
“አሁን ያለው መንግስት ጥዬ ስልጣን እይዛለሁ የሚለው አዲሱ ኃይልም ሆነ አሁን ስልጣን ላይ ያለው አካል የደቡብን ሕዝብ ድምጽ ችላ ማለታቸው አደገኛ አካሄድ ነው። የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ መንግስትን በመደገፉ ብቻ ወይስ የነሱ ፍላጎትና አጀንዳ ሰለባ ላለመሆን በመምረጡ ነው እንዲህ አይነት ስልታዊ መገለል የደረሰበት? የሚለው ጥያቄ በደንብ ሊታሰብበት ይገባል።”
“የደቡብ ኢትዮጵያ ምሁራን እና ፖለቲከኞች አሁን የሚደረጉም ሆነ ወደፊት የሚመጡ አገራዊ የፖለቲካ ለውጦች የደቡብ ኢትዮጵያን ሕዝብ ድምጽ እና ፍላጎት ያላካተቱ ከሆኑ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ፈጽሞ አይችሉም።
ማህበረሰባችን የሌሎች ፖለቲካዊ ፍላጎት መጫወቻ መሆን የለበትም፤ በመሆኑም ታሪካዊውን የማርጅናላይዜሽን ሂደት በመገንዘብ የደቡብ ኢትዮጵያን የፖለቲካ አቋም፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የህልውና ዋስትና በጠንካራ ሁኔታ ማስጠበቅ የሚችሉበትን አዲስ ስትራቴጂካዊ መንገድ መቀየስ ይጠበቅብናል።” ብለዋል።
Voice of Marginalized Community – WT Media