በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰሱ የዓለም ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ከተመዘገበ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ የሚገኘው የዎላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ ‘ጊፋታ’ በዓል በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እና በልዩ ልዩ ግዛቶች በሚኖሩ የዎላይታ ተወላጆችና ወዳጆች ዘንድ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

ከዚሁ በዓል ጋር ተያይዞ በአሜሪካ የቨርጂንያና ዋሽንግተን ዲሲ መካከል ከሚገኘው ታሪካዊው የግሬት ፓቶማክ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኙ የዎላይታ ተወላጆችና ወዳጆች፣ የዎላይታ የመጨረሻው ንጉሥ የካዎ ጦና ጋጋ የልጅ ልጅ እና የዎላይታ አስተዳዳሪ የነበሩትን ፊታውራሪ ደስታ ፍሥሐን (ሮቤ) በመቃብራቸው ስፍራ በመገኘት ዘክረዋቸዋል።

ፊታውራሪ ደስታ ፍሥሐ በአሜሪካ አገር ኖረው ያረፉ ሲሆን አስከሬናቸው ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት Woodrow Wilson (መቃብር ቁጥር #2176) አጠገብ በመቃብር ቁጥር #2146 ያረፈ ነው።

በመቃብራቸው ድንጋይ ላይም “DESTA FESSEHA (1903 – 1990) – SON OF WOLAITTA’S KING (ETHIOPIA)” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ይገኛል።
በስነ-ሥርዓቱ ወቅት ታዳሚዎቹ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ፊታውራሪ ደስታ ፍሥሐ ለዎላይታ ሕዝብ ባህል፣ ታሪክና ማንነት ያደረጉትን ታላቅ ተጋድሎ በክብር ያሰቡ ሲሆን የታሪክና የማንነት መሠረት የሆነውን የጊፋታን በዓል ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አፅንኦት መስጠታቸውን ከስፍራው ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።