GridArt_20260925_192610240

​በሰሜን ኢትዮጵያ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተባባሰ በመጣው የጸጥታ መደፍረስና የጦርነት ስጋት ሳቢያ፣ የውጭ ሀገር ዲፕሎማሲያዊ መሥሪያ ቤቶች ለዜጎቻቸው ጥብቅና ከባድ የደህንነት ማስጠንቀቂያዎችን ማስተላለፋቸውን ቀጥለዋል።

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ እና የካናዳ መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ባሉ አሳሳቢ የጸጥታ ሁኔታዎች ዙሪያ አዳዲስ መግለጫዎችን አውጥተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዛሬ አርብ መስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ባሰራጨው የደህንነት ማንቂያ መልዕክት፤ የአሜሪካ ዜጎች “በማንኛውም ምክንያት” ወደ አማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች እንዳይጓዙ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

ኤምባሲው በአማራ ክልል በላሊበላ ከተማ አቅራቢያ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የሚያመለክት መረጃ እንደደረሰው ገልጿል።

​ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትላንት ሐሙስ መስከረም 14 ጀምሮ ወደ ላሊበላ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን ኤምባሲው ጠቁሞ፤ ወደ ከተማይቱ የሚደረጉ በረራዎች ዳግም መቼ እንደሚጀመሩ እስካሁን መረጃ እንደሌለው አመልክቷል።

በአንጻሩ በጉዞ ማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ ባለው በትግራይ ክልልም የኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነት መቋረጡን የሚያመለክቱ መረጃዎች መድረሳቸውን ኤምባሲው በመልዕክቱ ላይ አክሎ ገልጿል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ወደሚገኙ አምስት ክልሎች ከሚደረጉ ማንኛውም ጉዞዎች እንዲርቁ ከዚህ ቀደም ለዜጎቿ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ የነበረችው ካናዳ፤ አሁን ላይ በዝርዝሩ ውስጥ የአፋር ክልል እንዲካተት አድርጋለች።

ካናዳ የአፋር ክልል የተካተተበትን አዲስ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ትላንት ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለአካባቢው መረጋጋት ከፍተኛ ስጋት መሆኑን አሳይቷል።

​በሰሜን ኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ እነዚህ ተከታታይ የጸጥታ መደፍረሶች እና የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች የሚያስተላልፏቸው ጥብቅ የጉዞ ማዕቀቦች ሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሰብአዊና ጸጥታዊ ቀውስ ምን ያህል ያህል የከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።