1000147969

​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሕግና ከስርዓት ውጭ በሆኑ አካሄዶች፣ በፖለቲካዊ ጫናዎች እና በግል ፍላጎቶች ሳቢያ ነጻነታቸው ተገፎ ከሚገኙ ዜጎች መካከል የወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ ጉዳይ የፍርድ ቤቶችን ነጻነት እና የፍትህ ስርዓቱን አሳሳቢነት በግልጽ የሚያሳይ ዋነኛ ማሳያ ሆኗል።

ባለሀብቱ ከክስ እና ከእስር ቤት ውጭ ሊያቆዩት ከሚገቡ በርካታ መሰረተ-ቢስ ክሶች ጋር ተያይዞ ከታሰረ አሁን ላይ ከአንድ ዓመት ከሶስት ወር በላይ አስቆጥሯል። በአሁኑ ወቅትም በጋሞ ዞን፣ በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት ውስጥ ፍትህ አጥቶ ይገኛል።

​WT Media ጉዳዩን በተመለከተ ከመጀመሪያው አንስቶ በቅርበት ሲከታተለው እና በመረጃ እና በተጨባጭ ሰነዶችን በመጠቀም እየዘገበ እንደቆየው በወጣቱ ባለሀብት ላይ የተከፈተው የክስ ሂደት ፍጹም ከህግ ውጭ በሆነ መልኩ በፖለቲካዊ ተነሳሽነት የተደረደረ ነበር።

በክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተለይም በርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ትዕዛዝ እና አቀንቃኝነት መጀመሪያ ላይ ባለሀብቱ ላይ “የ12 ቢሊዮን ብር የሙስና እና የገንዘብ ዝውውር ክስ” ተከፍቶባቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር።

​ነገር ግን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ እና አቃቤ ሕግ በቁጥጥር ስር ያዋሉት ወጣት ባለሀብት ላይ ያቀረቡት ግዙፍ የ12 ቢሊዮን ብር ውንጀላ ፍጹም መሠረት የሌለውና በሂደት ሲፈተሽ ውኃ የሚቋቋም ሆኖ ባለመገኘቱ ክሱ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ ወደ 53 ሺህ ብር ብቻ ዝቅ ሊል ችሏል።

ግዙፉ የ12 ቢሊዮን ብር ውንጀላ ከከሰሰ በኋላም የባለሀብቱን ነጻነት በግፍ በእስርቤት ለማስቀረት ሲባል “የዜይሴ ሕዝብ ያስታጥቃል” የሚሉ መሰረተ-ቢስ ወንጀሎች ሲደረደሩበት ቆይተዋል።

በመጨረሻም ክሶቹ ሁሉ መሠረት አጥተው ሲከሸፉ ባለሀብቱ ላይ የቀረበው ሌላው አስቂኝ እና አሳፋሪ ክስ “ለፖሊስ የቤት ቆጣሪ አስገብታሃል” የሚል ፍጹም ሕጋዊ ግብይትን ወንጀል የማድረግ ሙከራ ሆኖ መቅረቡ የፍትህ ስርዓቱ ወድቀት የየት ያህል አሳዛኝ ደረጃ ላይ እንዳለ ያሳያል።
​
​ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ በማህበረሰቡ ውስጥ ሰራ ፈጥሮ፣ ልማትን አስፋፍቶ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ተሳትፎ አድርጎ የነበረ ወጣት ባለሀብት ቢሆንም፤ በክልሉ ውስጥ ያሉ ፀረ-ልማት እና ጠባብ የፖለቲካ አጀንዳ አንቀሳቃሾች ባደረሱበት ተጽዕኖ ከአንድ ዓመት ከሶስት ወር በላይ ያለ ፍትህ በእስር ላይ ይገኛል።

​በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ወጣቱ ባለሀብት ያነሳቸው የሕግ ጥያቄዎች እና የነጻነት መብቶች በመንግስት አካላት ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለዋል።

ወጣት ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ክንፈ – by WT Media

የክልሉ ፍትሕ አካላት ሕግን አስከባሪነታቸውን ትተው የፖለቲካ መጠቀሚያ በመሆን በንጹህ ባለሀብቶች ላይ የሚፈጽሙት እንግልትና የበቀል እርምጃ በክልሉ ውስጥ እየሰፈነ ያለውን አምባገነናዊ አካሄድ በግልጽ ያሳያል።

ሕዝብንና ሀገርን ሊጠቅሙ የሚገባቸው ባለሀብቶችና ወጣቶች እንደ ወንጀለኛ ታስረው ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረጉ በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት ከባቢ አየር እና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል።
​
​ኢንጂነር ብርሃነመስቀል ያለምንም ፍትህ ለአንድ ዓመት ከሶስት ወር በላይ በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት መታሰሩ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍትህ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ በፖለቲካ ሰዎች ቁጥጥር ስር መውደቁን አመላካች ነው” በሚል የአከባቢው ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየጠየቁ ይገኛሉ።

WT Media የዚህን ወጣት ባለሀብት መብትና ነጻነት በተመለከተ ፍትህ እስኪያገኝ ድረስ ድምፁ ሆኖ መክረሙን ይቀጥላል።

የክልሉ መንግሥትና ኃላፊዎች በግል ጥቅምና በፖለቲካ ሴራ ላይ ተመስርተው በዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ኢ-ሕጋዊ እስር እና እንግልት በአስቸኳይ አቆመው ባለሀብቱ ያንዳች ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈታ አጥብቆ ይጠይቃል።

​Voice of Marginalized Community – WT Media