የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቀጣዮቹ ቀናት ይጨምራል ተብሎ በሚጠበቀው የዝናብ መጠን ሳቢያ የኮሌራ ወረርሽኝ ዳግም ሊከሰት እንደሚችል የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ። ተቋሙ በክልሉ በሚገኙ “ሁሉም አካባቢዎች” አደጋውን ታሳቢ ያደረገ አስቸኳይ የመከላከል እና የዝግጁነት ሥራ እንዲጠናከር ጥሪ አስተላልፏል። 

የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት የተላለፈው ለ12 የክልሉ ዞን ጤና መምሪያዎች እንዲሁም ለሶዶ፣ ዲላ እና አርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደሮች በሰፈረው ይፋዊ ደብዳቤ ነው። ባለፈው አርብ መስከረም 8 ቀን 2019 ዓ.ም. የተጻፈው ይህ ደብዳቤ፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከዓመታት በፊት የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ቀላል የማይባል የጤና ቀውስ እና የህይወት መጥፋት ማስከተሉን በውል አስታውሷል።

የአየር ንብረት ለውጥ እና የኤል-ኒኖ ስጋት በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በየትኛውም አካባቢ የኮሌራ ወረርሽኝ ያልተከሰተ መሆኑን የገለጸው የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ሆኖም ለበሽታው መከሰት ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ወረርሽኙ እንደገና ሊያገርሽ የሚችልበት ከፍተኛ አጋጣሚ እንዳለ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቁሟል።

ለዚህም በማስረጃነት የቀረበው የሜትዎሮሎጂ ትንበያ ሲሆን፤ በኢል-ኒኖ የአየር ንብረት ክስተት ምክንያት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የዝናብ ሁኔታ አሃዝ ከፍ እንደሚል ያሳያል። የፌደራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣው መረጃም፤ ኤል-ኒኖ በ37 ዞኖች ሥር በሚገኙ 178 ወረዳዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አጋልጧል። ኤል-ኒኖ በተለያዩ ሀገራት ድርቅን እና ጎርፍን ጨምሮ ከፍተኛ አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ይታወቃል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በቀጣዩቹ ቀናት እንደሚጨምር በሚጠበቀው የዝናብ ሁኔታ ሳቢያ የኮሌራ ወረርሽኝ ሊከሰት ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም በዚሁ የኤል-ኒኖ ክስተት ሳቢያ የሚከሰተው የተጋነነ ዝናብና የሚፈጠረው ጎርፍ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ምንጮችን በቀላሉ በመበከል ለኮሌራ ወረርሽኝ ማገርሸት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ በማስረጃ አስረድቷል። ለምሳሌነትም ደብዳቤው ከተጻፈላቸው ዞኖች አንዱ በሆነው በደቡብ ኦሞ በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ እንደነበር ይታወሳል።

ኮሌራን መገንዘብ እና ጥንቃቄ ማድረግ ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከትል፣ በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን ፈሳሽ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሟጥጦ በማስወገድ እና አካልን በማዳከም ለሕይወት አስጊ አደጋ የሚዳርግ ከባድ ተላላፊ በሽታ ነው።

በመሆኑም ህብረተሰቡ የንጽህና አጠባበቅ ደንቦችን በጥብቅ ሊተገብር እንደሚገባ፣ የሚመለከታቸው የጤና እና የአስተዳደር አካላትም ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የቅድመ ዝግጁነት እና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥበቃ ሥራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ WT Media አበክሮ ያሳስባል።

Voice of Marginalized Community – WT Media