በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ጋዘር ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የጋዘር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የሚከፈላቸው ደሞዝ የማይበቃ በመሆኑና ውዝፍ ደመወዛቸው በግዜ ባለመከፈሉ ከመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የጤና አገልግሎት መስጠት ማቋረጣቸውን በአቋም መግለጫ አሳውቀዋል።
የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ለ WT Media በላኩት የጋራ አቋምና ለሚመለከታቸው ያሳወቁት ደብዳቤ በተመለከተ እንደገለጹት፤ የ2018 ዓ.ም መስከረም ወር ውዝፍ ክፍያ፣ የሐምሌ ወር የዕረፍት ጊዜ (Duty) እና የነሐሴ ወር ደሞዝ በሥራ ላይ ለነበሩ ባለሙያዎች መከፈል ሲገባው ክልሉ ደሞዝ ከለቀቀ በኋላ እስከአሁን ድረስ ምንም ዓይነት ክፍያ አልተፈጸመም።

ባለሙያዎች ክፍያው እንዲፈጸምላቸው በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ከመንግሥት አካላት አንዳችም ምላሽ እንዳልተሰጠባቸው አስታውቀዋል።
የደሞዝ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ መዘግየቱ 30 ቀን ሞልቶ ተጨማሪ ሁለት ሳምንት በማለፉ ከመስከረም 6 እስከ መስከረም 8 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ክፍያው እንዲፈጸም ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ ባለማግኘቱ ከመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የጤና አገልግሎት ላለመስጠት መገደዳቸውን በመግለጫቸው አረጋግጠዋል።
በዚህ ውሳኔ ሳቢያ ለሚፈጠረው የአገልግሎት መስተጓጎል ባለሙያዎች ኃላፊነት እንደማይወስዱ እና የመንግሥት አካላት ኃላፊነቱን ሊወስዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
WT Media ከገለልተኛ ተገልጋዮች ባረጋገጠው መረጃ መሠረት በጋዘር ሆስፒታል ባለሙያዎች የሥራ ማቆር አድማ ሳቢያ የጤና አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በመስተጓጎሉ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል።
የዜናው አካል የሆነውን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እና የተቋሙን ሠራተኞች ፊርማ የያዘውን መረጃ WT Media ተመልክቷል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የሚመለከታቸውን የክልሉን እና የዞኑን ኃላፊዎች ለማነጋገር የተደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ይሁን እንጂ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በየቦታው የሚታየው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ መዘግየትና አስተዳደራዊ ቸልተኝነት ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ ሲሆን ከዚህ ቀደም በ WT Media እንደተዘገበው መሰል ችግሮች የመንግሥት ሠራተኞችን ለከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረጉዋቸው ይገኛሉ።
Voice of Marginalized Community – WT Media