1000149120

​በበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መኖሪያነት በሀገሪቱ 3ኛ ትልቅ ክልል ከሚሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ጥላሁን ከበደ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል።

አቶ ጥላሁን ከክልል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ ዝቅ ተደርገው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ተሹመዋል። በክልሉ አሁን ላይ በተፈጠረው ክፍተት መሰረት፣ አዲስ ፕሬዚዳንት በነገው ዕለት በሚካሄደው ምክርቤት ስብሰባ እንደሚመረጥ ይጠበቃል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በድንገት ከኃላፊነት መነሳታቸውን ተከትሎ በክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ፣ በፕሬዚዳንት ቢሮ እና በገቢዎች ቢሮ ውስጥ ሰነድ የማጥፋት እና የማጋየት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች በስፋት እየተካሄዱ መሆኑን ከስፍራው ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

አቶ ጥላሁን ከበደ

በቁልፍ ቢሮዎች ላይ የተጀመረው ይህ የሰነድ ማጥፋት ዘመቻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልሉ አካላት አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት በማድረግ በተመረጡ ቢሮዎች ላይ አፋጣኝ የጊዜያዊ እግድ እና የቁጥጥር ሥራ እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል።

​የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ጠንካራ አቋም አንጸባርቀዋል፤ “ሕገ-ወጥ ሆኖ የተገኘ ንብረት ማስመለሻ አዋጅ ቁጥር 1360/2025 መሠረት በማድረግ ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅር ውስጥ በፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ሕግ እና በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጥብቅ ምርመራ ሊጀመር ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

በክልሉ ሕግ እንዲከበር እና ሕገ-መንግስታዊነት እንዲረጋገጥ የህግ አስከባሪ አካላት ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ የህብረተሰቡ ክፍሎች አጥብቀው እየጠየቁ ይገኛሉ።

አቶ ጥላሁን ከበደ በቆይታቸው “በኢፍትሃዊነት፣ በሌብነትና እርስበርስ መጠራጠር በመፍጠር አወሳስበው የሄዱትን ክልል መልሶ ማደራጀትና ማስተካከል ጠንካራ አመራር ይሻል” በሚል በርካቶች ሲተቿቸው ቆይተዋል።

WT Media ከዚህ ቀደም እንደዘገበው በክልሉ በየቦታው የሚታዩ የደሞዝ መዘግየቶች፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሌብነት እና የተንሰራፋው አስተዳደራዊ ቸልተኝነት የህዝብን ቅሬታ ሲያባብሱ ቆይተዋል።

​አሁን ላይ የተደረገው የአመራር ለውጥ እና እየተፈጸሙ ያሉ የሰነድ ማጥፋት ድርጊቶች ክልሉ የገባበትን ጥልቅ ተቋማዊ ቀውስ በግልጽ ያሳያሉ። WT Media በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ አዳዲስ ወቅታዊ መረጃዎችን እና የሰነድ ማጥፋት ስጋቶችን በቅርበት የሚከታተል ይሆናል!

​Voice of Marginalized Community – WT Media