በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን እና በገረሴ ወረዳ (በኮሻሌ ቀበሌ) በአርሶ አደሮች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳው ከፍተኛ የመሬት ይዞታ ውዝግብ እና ግጭት የበርካታ የጸጥታ አባላት እና ንጹሃን ሕይወት ማለፉ ተገልጿል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ከተለያዩ ወገኖች የደረሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግጭቱ የከፋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች ለዘመናት አርሶ ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬት የዞኑ እና የወረዳው አመራሮች (ከቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና ከአለማየሁ አበራ ጋር በመቀናጀት) “ኦሞቴክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ” ለተባለው ድርጅት በኢንቨስትመንት ስም ለመስጠት በመሞከሩ ውዝግቡ ማገርሸቱ ታውቋል።
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚሰማሩበት የመስኖ ማስተላለፊያ እንዳይሄድ በመታገዱና ከመሬታቸው እንዲፈናቀሉ በመደረጉ ቅሬታቸውን ሰስተው እስከ ፕሬዚዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ ቢሮ ድረስ ለአቤቱታ ሄደው እንደነበር ተገልጿል።

ይሁን እንጂ አመራሮቹ አቤቱታውን ተቀብሎ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ “አርፋችሁ ካልተቀመጣችሁ ትጠፋላችሁ” በማላት ማሸማቀቃቸውን እና ህዝቡን በዞኑና በወረዳው የጸጥታ መዋቅር ሲያስገርፉና ሲያሳስሩ ቆይተዋል የሚሉ ከባድ ውንጀላዎች ቀርበዋል።
ከዚህም በላይ በዚህ የኢንቨስትመንት ስራ ምክንያት አንድ ቤተክርስቲያን እና አንድ ትምህርት ቤት ጭምር ከነባር ቦታቸው ተነሺ መሆናቸው ተመላክቷል።
ባለሀብቱ መሬቱን ለማልማት ባሰማራቸው ማሽነሪዎች እና ሰራተኞች ላይ ነዋሪዎቹ ተኩስ በመክፈት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ሁኔታውን በኃይል ለመቆጣጠር የገቡት የዞኑ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል።
በግጭቱ አሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የገረሴ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር መስከረም 21 ቀን 2019 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ ከገረሴ ከተማ 3 የፖሊስ አባላት፣ ከገረሴ ዙሪያ ወረዳ 4 የፖሊስ አባላት እና 2 ሚሊሻዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 9 የጸጥታ አባላት ሕይወት ማለፉን ይፋ አድርጓል።
ከግጭቱ ሰለባዎች መካከልም ዋ/ሣጅን ዮሴፍ ኡማቶ በሆስፒታል ሕክምና ላይ እያለ ሕይወቱ ማለፉ ቀደም ሲል መረጋገጡን ከትናንት በስቲያ WT Media መዘገቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ከ WT Media የደረሱ ሌሎች አማራጭ ምንጮች እና የምርመራ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የሟቾች ቁጥር ከቀረበው መግለጫ በላይ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።
በጋሞ ዞን ገረሴ ዙሪያ ብቻ 10 መደበኛ እና 2 ከመከላከያ የተቀነሱ አባላትን ጨምሮ በርካቶች በጥይት ተመተው ሕይወታቸው ማለፉን፣ እና ከሰኞ ዕለት ጀምሮ የወደቁ አስክሬኖች ሳይነሱ መቆየታቸው ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መፈጠሩን ያመለክታሉ።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ አካባቢው ገብተው የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ ቢሆንም፣ ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም አልተመለሰም።
በሰፈረው ውጥረት ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጭስ ቦምብ ጭምር መወርወሩን እና በቁጥር በውል ያልታወቁ ንጹሃን ዜጎች በጸጥታው አካላት መገደላቸው ተገልጿል።
በጋሞ ቆላማ ወረዳዎች ላይ መሰል ግጭቶች እና መሬት ነጠቃዎች እንዳይባባሱ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠ በቀር፣ አሁንም ተጨማሪ ግጭቶች ለመፈንዳት አኮብኩበው እንደሚገኙ መረጃዎች ያስጠነቅቃሉ። WT Media በጉዳዩ ዙሪያ ያሉትን ተጨማሪ መርመራዎች እና የተሟላ መረጃዎች ለአንባቢያን ማድረሱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
Voice of Marginalized Community – WT Media