IMG_20261009_161119_949

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ፤ኢህአፓ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ የታሰሩ እና «መንግስት ያቀረበውን የይቅርታ ሰነድ አንፈርምም» ብለው በቀሩ እስረኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ሰዎች እና የማህበረሰብ አንቂዎች ላይ «ከፍተኛ ግፍ፣ ጫና እና እንግልት» እየደረሰ መሆኑን አመልክቷል።

በእስር ቤቶች የሚፈጸሙ ማንኛውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እና ሕጋዊ መሠረት ሳይኖር የተያዙ ሰዎች በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቋል።

«ከተራዘመ የእስር ጊዜ በኋላ ግማሾቹን እስረኞች በቅደመ ሁኔታ ፈትቶ ሌሎቹን በእስር የማቆየት ከፋፋይ ተግባር ነው» ሲል ተግባሩን በፅኑ እንደሚያወግዝ ገልጿል።

እስረኞች ካሉበት እስር ቤት በማስወጣት ለየብቻ ማቆየት፣ ንጽህና በጎደለውና ለሰው ልጅ በማይመጥን ሁኔታ ውስጥ ማስቀመጥ፣ ወደ ማይታወቁ ስፍራዎች ማዛወር እና ዛቻዎች በፍጹም በዝምታ ሊታለፉ የማይገባቸው ከባድ የመብት ጥሰቶች ናቸው ሲልም ፓርቲው ገልጿል።

በማቆያ ማዕከላት የሚደርሱ የእስረኞች አያያዝ፣ የጤና ሁኔታ፣ የንጽህና ሁኔታ እና የሕጋዊ መብቶቻቸው ጉዳይ በነጻና ገለልተኛ አካላት እንዲመረመሩ አሳስቧል።

«ፖለቲካዊ አቋም ወንጀል አይደለም» ያለው ፓርቲው የተለየ አስተሳሰብ በሀሳብ መሞገት አለበት በማለት ገልጿል።

ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተሳታፊዎችና የማህበረሰብ አንቂዎች ሙያቸውንና ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ የሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ፓርቲው ጥሪ አድርጓል።