የደቡብ ኦሞ የጉዞ እፎይታ የነበረው የጅንካ-ጎፋ-ዎላይታ ሶዶ አቋራጭ መንገድ በመሰረተ ልማት መፍረስ ምክንያት ሊቋረጥ መሆኑ በአከባቢው ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩ ተነግሯል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጅንካ በጎፋ አድርጎ ወደ ዎላይታ ሶዶ የሚወስደውና የደቡብ ኦሞ ዞን ማኅበረሰብን የጉዞ እንግልት የቀነሰው አቋራጭ መንገድ በድልድዮች መፍረስ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ስጋታቸውን ለ WT Media ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ከጅንካ ወደ ዎላይታ ሶዶ በአርባ ምንጭ በኩል የሚደረገው ጉዞ ሁለት ቀናትን ይወስድ የነበረ ቢሆንም በጎፋ በኩል የተዘረጋው መንገድ ጉዞውን ወደ አንድ ቀን በማሳጠር ለቀጣናው ማኅበረሰብ ከፍተኛ እፎይታ ሰጥቶ መቆየቱን ተጠቃሚዎች አስረድተዋል።
ነገር ግን እንደ መረጃ ምንጮች ገለጻ በሰነጋል ተራራ መውረጃ በኩል ያለው አንድ ድልድይ በመሰበሩ ምክንያት የሰነጋል መስመር መንገድ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

በቃቆ በኩል ደግሞ በማሊ አቅጣጫ የሚገኘው አንደኛው ድልድይ በውኃ ሙላት በመወሰዱ ምክንያት አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪዎቻቸውን በውኃ ውስጥ አያሳለፉ ለመጓዝ ተገደዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ክረምትና የዝናብ ወቅት በመጀመሩ ምክንያት ተሽከርካሪዎች በውኃ ውስጥ ማለፍ የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው የመንገድ መስመሩ ሙሉ በሙሉ የመቋረጥ አደጋ መደቀኑንም ጠቁመዋል።
ይህ መንገድ ሙሉ በሙሉ የሚቋረጥ ከሆነ በተለያዩ የክልል ቢሮዎችና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሠሩ አካላት፣ ለንግድና ለሕክምና ጉዳይ ወደ ዎላይታ ሶዶ እና ሐዋሳ የሚጓዙ ዜጎች ለከፍተኛ ተጨማሪ ወጪና እንግልት እንደሚዳረጉ ይገለጻል።
የመንገዱ መስተጓጎል በአካባቢው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የክልሉ መንግሥትና የሚመለከታቸው የመሰረተ ልማት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የተጎዱትን ድልድዮች በአስቸኳይ መልሰው እንዲገነቡ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
WT Media በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
Voice of Marginalized Community – WT Media