Foreign Press Association Condemns Brief Detention and Release of Journalists Samuel Getachew and Amanuel Gebremedhin

የአፍሪካ የውጭ ሀገራት ፕሬስ ማህበር ኢትዮጵያዊ-ካናዳዊው ጋዜጠኛ ሳሙኤል ጌታቸው እና የኤሶሼትድ ፕሬስ (AP) ጋዜጠኛና ቪዲዮግራፈር አማኑኤል ገብረመድህን ብርሃኔ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ታስረው ለስምንት ቀናት መቆየታቸውን አጥብቆ ማኮነኑን አስታወቀ።

ሁለቱም ጋዜጠኞች መስከረም 22 (ኦክቶበር 2) በቁጥጥር ስር የዋሉት በትግራይ ክልል ያለውን የማህበራዊና የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከሚያደርጉት የጋዜጠኝነት ስራ እና ዘገባ ጋር በተያያዘ እንደነበር ተገልጿል። ለስምንት ቀናት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ጥቅምት 1 (ኦክቶበር 10) ከእስር ተለቀዋል።

ጋዜጠኛ ሳሙኤል ጌታቸው ከእስር ከተፈታ በኋላ ባስተላለፈው መልእክት ከእስር እንዲወጣ በዲፕሎማሲያዊና በህግ መንገድ ጥረት ላደረጉ ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ ምስጋናውን አቅርቧል፦ “ከአስር ቀናት በፊት ታስሬ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ተፈትቻለሁ… አሁንም የጋዜጠኝነት ስራዬን በነፃነትና በደህንነት የምሰራበት ቦታ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።

ማህበሩ የጋዜጠኞቹን መፈታት ቢደግፍም መታሰራቸው ያሳደረውን አሉታዊ ተጽእኖ እንደማያቀለው ገልጿል። በተለይም በግጭትና በፖለቲካዊ ውጥረቶች ወቅት የፕሬስ ነፃነትና የጋዜጠኞች ደህንነት መከበር ያለበት መሰረታዊ መብት መሆኑን አሳስቧል።

“ጋዜጠኝነት በጭራሽ ወንጀል አይደለም። ማንኛውም ጋዜጠኛ ስራውን በመስራቱ ብቻ ሊታሰር አይገባም” ያለው የማህበሩ መግለጫ፣ “እንዲህ ያሉ እገዳዎችና እስሮች ያለተጠያቂነት እንዲቀጥሉ መተው በፍርሃት የተሞላና እራስን በራስ የመቆጣጠር (Self-censorship) መንፈስን በመፍጠር በግልጽነትና በዲሞክራሲ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል” ሲል ገልጻል።

የአፍሪካ የውጭ ሀገራት ፕሬስ ማህበር የኢትዮጵያ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት የህግ የበላይነትንና የፕሬስ ነፃነትን በማክበር፣ ሀገር በቀልና አለም አቀፍ ጋዜጠኞች ያለእስራት፣ ማስፈራሪያና ጥቃት ስራቸውን በነፃነት እንዲሰሩ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ጥሪ አቅርቧል።