ባለሀብት ብርሃንመስቀል ክንፌ

ወጣቱ ባለሀብት ብርሃንመስቀል ክንፌ በእስር ላይ እንዳሉ አሁንም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት እግድ በጣለበት ቦታ ላይ ሕገ-ወጥ የሀብት ማሸሹ ተግባር መቀጠሉ ተገልጿል።

​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ቦሮዳ ወረዳ በሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማዕድን ቦታ ላይ የተፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችንና የሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ WT Media በተደጋጋሚ ዘገባዎችን ማቅረቡ ይታወቃል።

​ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወጣቱ ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃንመስቀል ክንፌ በቀድሞ የአካባቢው አመራሮች ተጽዕኖና አፍኖ በማሰር እርምጃ ከተወሰደበት በኋላ ከአንድ ዓመት ከግማሽ በላይ ቤተሰቡ ካለበት ሩቅ ቦታ ተወስዶ በአርባምንጭ ማረሚያ ቤት ይገኛል።

 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን የመፍቻ ትዕዛዝ እና የፌደራል ፖሊስ ትዕዛዙን ለማስፈጸም ያደረገውን ጥረት አካባቢው ላይ በነበረው አደረጃጀት ምክንያት ሳይፈጸም መቅረቱ የሚታወስ ነው።

​ለባለሀብቱ እስርና እንግልት እንደ ዋነኛ መንስኤ የሚጠቀሰው መብቱን ለማስከበር በሕግ መንገድ ወደ ፍርድ ቤት ከሄደ በኋላ በብሔራዊው የፌደራል ሚዲያ (ፋና ቴሌቪዥን) ላይ በቦታው የነበረውን ብልሹ አሰራርና የሀብት ምዝበራ የሚያጋልጥ የምርመራ ዶክመንተሪ አዘጋጅቶ ለአየር ማብቃቱ ነው።

ወጣቱ ባለሀብት ኢንጂነር ብርሃንመስቀል ክንፌ

 ይህ አጋላጭ ዶክመንተሪ በብዙኃን ዘንድ ከተመለከተ በኋላ ጥቅም የተነኩ የአካባቢው አመራሮች ባለሀብቱን አፍነው በማሰር ከአንድ ማረሚያ ቤት ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት፣ ከፍርድ ቤት ወደ ፍርድ ቤት ሲያዛውሩት ቆይተዋል።

​የሕግ ምንጮች እንደሚጠቅሱት ባለሀብቱ እዛው ማረሚያ ቤት እንዲቆይና የኢንቨስትመንት ሥራው እንዲስተጓጎል ለማድረግ የቀድሞ አመራሮች እስከ 12 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የፈጠራ ክስ ሳይቀር አዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም ክሱ በሕግ ፊት ተቀባይነት አጥቶ ውድቅ ተደርጓል። 

ነገር ግን እነዚህ አካላት አንዱ ክስ ውድቅ ሲሆን ሌላ የሀሰት ክስ እያደራረቡ በማቅረብ፣ ባለሀብቱ ሕጋዊ የዋስትና መብቱን እንኳ አግኝቶ እንዳይወጣ በማድረግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የስነ-ልቦና ጫና እያደረሱበት ይገኛሉ።

​በቅርቡ በክልሉ ከፍተኛ የአመራር ለውጥ የተደረገ ቢሆንም በሕጋዊ መንገድ ለኢንጂነር ብርሃንመስቀል ክንፌ ይገባው በነበረውና የፌደራል ፍርድ ቤት የዕገዳ ውሳኔ ባስተላለፈበት የማዕድን ቦታ ላይ አሁንም ሕገ-ወጥ የድንጋይ ከሰል ማውጣትና ማሸሽ ሥራዎች በቀጣይነት እየተካሄዱ መሆኑን የአካባቢው የመረጃ ምንጮችና ባለሀብቶች ለ WT Media አስታውቀዋል።

​እንደ ምንጮቹ ገለጻ ከዚህ ቀደም ቦታውን በሕገ-ወጥ መንገድ ነጥቀው የወሰዱ አካላት ባለሀብቱ በማረሚያ ቤት በግፍ እንዲቆይ በማድረግ በየቀኑ በርካታ መኪናዎችን በመጫን የድንጋይ ከሰል ሀብቱን እያሸሹ ይገኛሉ።

እነዚህ አካላት ለመንግሥት መከፈል ያለበትን የግብር ገቢ ሳይከፍሉ እና ቀደም ሲል WT Media ባጋለጠው ዓይነት በሐሰተኛ ደረሰኞችና አሰራሮች በመጠቀም የተፈጥሮ ሀብቱን እያባከኑ ይገኛሉ።

በአካባቢው አዲስ የለውጥ አየር በመምጣቱና የቀድሞው በግፍ የታሰረው ባለሀብት ይፈታል የሚል ትልቅ ተስፋ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን በሀሰተኛ ክሶች መደራረብ ምክንያት ሳይፈታ መቆየቱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቅሬታና ክርክር ፈጥሯል።

​የፌደራል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እያለና ቦታው በሕግ እገዳ ስር እንዲቆይ ተወስኖ እያለ ባለሀብቱ በሀሰተኛ ክሶች በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጎ እነዚህ አካላት የማዕድን ምርቱን ለማውጣትና ለመሸጥ እንዴት ሕጋዊ ሽፋን አገኙ? የመንግሥት የግብር ስርዓትስ በግልጽ እየተጣሰ እንዴት ዝምታ ተመረጠ? የሚሉት ነጥቦች በአካባቢው ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ዘንድ አጣዳፊ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች ሆነዋል።

​የክልሉ አዲስ አመራር በልማትና በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የጀመረውን የማጽዳትና የሕግ የበላይነት የማስከበር እርምጃ በዚህ በጋሞ ዞን የሮዳ ወረዳ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ቦታ ላይም በመተግበር በሀሰተኛ ክስ የታሰረውን ባለሀብት ሰብአዊና ሕጋዊ መብት እንዲያስከብር እንዲሁም እየተካሄደ ያለውን ሕገ-ወጥ የሀብት ብዝበዛ በአስቸኳይ እንዲያስቆም ጥሪ ቀርቧል።

​WT Media በጉዳዩ ዙሪያ የተወነጀሉትን አካላት እና የሚመለከታቸውን የፍትሕና የማዕድን ቢሮ ኃላፊዎችን ምላሽ ለማካተት የሚያደርገውን ሙያዊ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።