የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኑሪዬ ሱሌ ዛሬ ሃላባ ላይ በተጀመረዉ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት በዘንድሮ ዓመት ብቻ በክልል ተቋማት ደረጃ ባሉት የስነምግባርና ፀረ ሙስና ዳሬክቶሬቶች በተቋሞቻቸዉ በተለያየ መንገድ የተመዘበረ የህዝብና የመንግስት ሃብት 20,550,633.49 በላቀ ትግል ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ እንዲሆን ማስቻላቸዉን ተናግረዋል፡፡
የተመዘበረዉን የህዝብ ሃብት ተመላሽ ከማድረጉም በተጨማሪ 77,167,342 ከ15 በተለያየ የሌብነት እና የማጭበርበር ስልት ከመንግስት ካዝና ሊወጣ የነበረ የህዝብ ሃብት በአስቸኳይ መከላከል ስራ ሳይመዘበር የማዳን ስራ ተሰርቶበታል፡፡
በዞኖች እና በሥር መዋቅሮች በተለያየ ምክንያት ሊመዘበር የነበረና የዳነ 133,171,509.19 የመንግስትን የህዝብ ሃብት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ቡድን መሪዎች ጠንካራ ትግልና ክትትል በማድረግ በቅድመ መከላከል የማዳን ሥራ ሰርተዋል፡፡
ከመከላከል ስራዉ ባሻገር በተለያየ መንገድ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተመዝብሮ የነበረን 77,305,557.91 ክትትል በማድረግ ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ እንዲደረግ በዞኖች፣ በልዩ ወረዳዎች እና በወረዳዎች በሚገኙ የተደራጁ የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ቡድን መሪዎች በባለቤትነት መንቀሳቀሳቸዉን ነዉ ኮሚሽነር ኑሪዬ የጠቆሙት፡፡
ኮሚሽኑ ራሱ በደረሰዉ ጥቆማ መነሻ ተንቀሳቅሶ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ የህዝብና የመንግስት ሃብት ከምዝበራ አድኗል፡፡ የዚህ ሁሉ ገንዘብ ሽርፍራፊ ሳንቲም ሳይቀር ገቢ የተደረገበት ደረሰኝ ተያይዞበታል፡፡
ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ የተመዘበረ ገንዘብ ብቻ አይደለም ያስመለሰዉ ይላሉ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኑሪዬ ሱሌ፡፡ በሌብነት ሰንሰለት ተሰናስለዉ ከመንግስት ተቋማት የተዘረፉትን በርካታ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የመንግስት ንብረቶችም ተመላሽ አስደርጓል፡፡
ከትራንስፎርመር እስከ ጀነሬተር፤ ከከተማ መሬት እስከ ገጠር የወል መሬት፤ ከሞተር ሳይክል እስከ ነዳጅ ስርቆት፤ ከላፕቶፕ እስከ ዉሀ ፓምፕ፤ የጂፒኤሶች እና ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ሌብነት፤ ህገ ወጥ ቅጥርና ዕድገትን ጨምሮ አይን ያወጣ በዉሎ አበል ስም የተዘረፈ የህዝብና የመንግስት ሃብት በኮሚሽኑ ታላቅ ተጋድሎ ወደ መንግስት ካዝና ገቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ካለዉ ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊት መበራከት፤ ከተንሰራፋዉ ብልሹ አሰራርና የመንግስት ሃብትና ንብረት ብክነት አንፃር ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካት ጋር ተቀናጅቶ መስራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉት ኮሚሽነር ኑሪዬ ሱሌ በተደራጀ መልኩ የመልካም ስነ-ምግባር ግንባታንና ብልሹ አሰራር ትግልን ህዝባዊ መሰረት አስይዞ መምራት እንደሚገባ ያሰምሩበታል ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዝርዝር ወቅታዊ፣ ትኩስ እንዲሁም ሚዛናዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ዌብሳይት
www.wolaitatimes.com.et
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/wolaitatime/
ቴሌግራም፦
https://telegram.me/Kiikiya
ዩቲዩብ፦
https://m.youtube.com/channel/UCQy9hoOijiE8FStts2SmtXw?noapp=1
በመጠቀም መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል።
Wolaita Times, 14/12/13 E.C , Sodo, Ethiopia🇪🇹


