የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14 (2/ለ) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ባስተላለፈው ውሳኔ፣ የኢፌዴሪ መንግሥት በትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት መሥረት ነው ተብሏል።
ይህ የተቋቋመው የባለአደራ አስተዳደር ለሚቀጥሉት 6 ወራት ክልሉን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም በክልሉ የተረጋጋ የፖለቲካና የሰላም ሁኔታን በመፍጠር፣ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ነፃና ግልጽ ምርጫ ተካሂዶ ትግራይ የፌዴሬሽኑ መደበኛ አካል የምትሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሆነ ተገልጿል።


የባለአደራ አስተዳደሩ ዋና ዋና ተግባራትና ኃላፊነቶች ከፌዴራል የመከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት እንዲሁም ከትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ከክልል እስከ ቀበሌ የተረጋጋ ሁኔታ መፍጠር፣ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱና ተሐድሶ እንዲያደርጉ ማመቻቸት፣ እንዲሁም የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደ አዲስ ማደራጀት የሚለው ይገኝበታል።
እንዲሁም የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ በመዘርጋት ሕዝቡ መደበኛና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር፤ በጦርነቱ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን ወደ ሥራ ማስገባት እና የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደየቀያቸው መመለስ፤
ሰላማዊና አካታች ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ የሕዝብ መድረኮችንና የሚዲያ ሥራዎችን ማስተባበር ናቸው።
ባለአደራ አስተዳደሩ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ የዕለት ተዕለት አገልግሎቶችን ከማቅረብ ባሻገር ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ ውሳኔዎች ላይ እንደማይንቀሳቀስና ተግባሩንም ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት እንደሚያከናውን ተጠቅሷል።
በዚሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለባለአደራ አስተዳደሩ የሚከተሉትን ዋና አስፈጻሚዎች ሹሟል፦
አቶ አሰፋ አብርሃ ሐጎስ፦ የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ
ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ ወ/ሥላሴ፦ የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ
ብሪጋዴር ጄነራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ ኃይሉ፦ የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ
አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወ/ሥላሴ፦ የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ
ዶክተር ሽሻይ አማረ፦ የመቐለ ከተማ ከንቲባ
የፌዴራል መንግሥቱ ለተሾሙት አመራሮች አስፈላጊውን መመሪያ፣ አቅጣጫ፣ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግላቸው መሆኑ ተገልጻል።