1000153561

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ቶጃ ስቤ ቀበሌ ከመብራት ትራንስፎርመር ዝርጋታ ጋር ተያይዞ የተከሰተን አለመግባባት ለማረጋጋት በተሰማሩበት ወቅት በደረሰባቸው ጥቃት የረ/ኢንስፔክተር ሚልክያስ ዳንኤል ህይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

​እንደ ወረዳው ፖሊስ መረጃ፤ አደጋው የደረሰው ጥቅምት 5 ቀን 2019 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ላይ ሲሆን፣ ረዳት ኢንስፔክተር ሚልክያስ ከአካባቢው ማኅበረሰብ በወጡ ሕገ-ወጥ አካላት በድንጋይ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።

​በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ የወንጀል መከላከል ቡድን መሪ እና የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ በመሆን ያገለገሉት ረዳት ኢንስፔክተር ሚልክያስ ዳንኤል፣ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የነበሩ ሲሆን የሁለተኛ ልጃቸውን መወለድ በጉጉት ይጠብቁ እንደነበር ተገልጿል።

​የደምባ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በሰራተኛው ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጾ፣ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ መጀመሩን አስታውቋል። ፖሊስ አክሎም የአካባቢው ማኅበረሰብ ወንጀለኞችን ለጸጥታ አካላት በመጠቆምና አሳልፎ በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ የረ/ኢንስፔክተር ሚልክያስ ዳንኤል አሳዛኝ ህልፈት እና ከዚህ ቀደም በጋሞ ዞን ገረሴ አካባቢ ከመሬትና ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ በሕዝብና በጸጥታ አካላት መካከል በተከሰተው ግጭት የብዙ ወገኖቻችን (የፖሊስ አባላትና የአካባቢው አርሶ አደሮች) ሕይወት ማለፉ ትልቅ የሕሊና ቁስል ሆኖ አልፏል።

​እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች የሚያስተላልፉት አብይ መልዕክት፦ ከማኅበረሰቡ ፍላጎትና እምነት ውጭ በኃይልና በስሜት የሚደረጉ የሕግ ማስከበርም ሆኑ የልማት እንቅስቃሴዎች የከፋ እልቂትና የሰው ሕይወት ጥፋት ማስከተላቸውን ነው።

​በመሆኑም የመንግሥትና የጸጥታ አካላት ከአካባቢው ሕዝብ ጋር የሚነሱ አለመግባባቶችን (የመብራት፣ የመሬት፣ የልማትና የሌሎች መሰረተ ልማት ጥያቄዎችን) በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፦ በግልጽነትና በቅንነት ሕዝቡን በማወያየትና በማሳመን መፍትሔ መስጠት፤

​የማኅበረሰቡን ቅሬታዎች አስቀድሞ በመስማት የችግሮችን መነሻ በሰላማዊ መንገድ ማጥፋት፤

​የጸጥታ አካላት ሕይወትም ሆነ የዜጎች ሕይወት በከንቱ እንዳይቀጠፍ ጥንቃቄ ማድረግ፤ እንደሚገባቸው WT Media በአጽንኦት ያሳስባል።

​የሕግ የበላይነት የሚከበረው የሕዝብን አመኔታ በማተርና የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ እንጂ ተጨማሪ የሰው ሕይወት በማጣት ሊሆን አይገባም።