ቀደም ሲል ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ይዘቶችን በማሰራጨቱ ምክንያት የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃዱ ተሰርዞ የነበረው “ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት”፣ በ”ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” አዲስ ስያሜ የብሮድካስት ፈቃድ እንደተሰጠው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ ይፋ ባደረገው መግለጫ እንዳመለከተው፣ የጣቢያው ፈቃድ ተሰርዞ የነበረው በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር ሕገወጥ ይዘቶችን ሲያሰራጭ በመገኘቱ ነበር።
ሆኖም የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ጣቢያው ቀደም ሲል የጦርነት መሳሪያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ፈቃዱ መሰረዙን አውስቶ፣ አሁን ግን የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በሚል ጥያቄ ማቅረቡ ተገልጿል።
ባለአደራ አስተዳደሩ የስያሜ ለውጥ በማድረግ ጣቢያው “ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” በሚል አዲስ ስያሜ ተቀይሮ ፈቃድ እንዲሰጠው ያቀረበውን ጥያቄ ባለሥልጣኑ ከመገናኛ ብዙኃን አዋጁ አንፃር መርምሮ ተገቢ መሆኑን በማመን ተቀብሎታል።
ስለሆነም ባለሥልጣኑ ለጣቢያው አዲስ የብሮድካስት ፈቃድ መስጠቱን ያስወቀ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለብሮድካስት አገልግሎቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።