1000157994

በዘይሴ ብሄረሰብ ላይ እየተፈጸመ የነበረው “የዘር ማጥፋት” ዘመቻ የክልሉ አመራር ለውጥ ተከትሎ አንፃራዊ መረጋጋት ቢፈጥርም የተጋረጠው ሰብአዊ ቀውስ አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ነዋሪዎች አሳስበዋል።

​በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የዘይሴ ቀበሌዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት ከመዋቅርና ከልዩ ወረዳነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በብሔረሰቡ አባላትና በክልሉ መንግሥት መካከል በተፈጠረ ውጥረትና ግጭት ሳቢያ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱ ይታወሳል።

WT Media ከግጭቱ መጀመሪያ ጀምሮ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታና የንጹሃን ዜጎችን ሰቆቃ በየጊዜው በቅርበት ሲከታተልና ሲዘግብ መቆየቱ ይታወቃል።

​በአሁኑ ወቅት ከኮሬ፣ ከቡርጂ፣ ከኮንሶ፣ ከዴራሼ፣ ከጋሞ፣ ከጋንታ ዴሬ እንዲሁም ከዘይሴ ቀበሌዎች የተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች ባካሄዱት የባህላዊና ማህበራዊ እርቅ ጥረት በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መስፈን ቢችልም፣ የችግሩ ስረ-መሰረት በሆኑት የመዋቅር፣ የፖለቲካና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ላይ የሚታዩ ድክመቶች ቀውሱን አሁንም አያበቃውም የሚል ጥልቅ ስጋት ደቅነዋል ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
​
​ከአንድ ወር በፊት በአገር ሽማግሌዎች ጥረት የተገኘውን ሰላም ተከትሎ በበርካታ የዘይሴ ቀበሌዎች የመማር ማስተማር ሂደት መጀመር ቢችልም፣ በዘይሴ ደንብሌ ቀበሌ በሚገኘው ኦጎሌ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግን እስካሁን ትምህርት አልተጀመረም። ለዚህም ዋናው ምክንያት በግጭቱ ሳቢያ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውና ከቀያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ነዋሪዎች ትምህርት ቤቱን እንደ ጊዜያዊ መጠለያ በመጠቀማቸው ነው።

በዘይሴ ደንብሌ ቀበሌ በሚገኘው ኦጎሌ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

​በዚህም ምክንያት የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሁለተኛ ወር ጥቅምት አጋማሽ ላይ በተደረሰበት በአሁኑ ወቅት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል። በአሁኑ ወቅት በዘይሴ ደንብሌ፣ በንዑስ ዘንሴ፣ በማዤ እና በኦጎሌ ቀበሌዎች የሚገኙ በርካታ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቱ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ የማዤ ንዑስ ቀበሌ ነዋሪዎች “ልጆቻችን እንደ ሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎች በአስቸኳይ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አለባቸው” ሲሉ ለ WT Media በቁጭት ገልጸዋል።

​የአገር ሽማግሌዎች በእርቅ ሂደቱ ወቅት በቅድሚያ የተፈናቃዮች የመልሶ ማቋቋም ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ በተግባር ግን እስካሁን ምንም አይነት የሚታይ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ነዋሪዎች ይጠቁማሉ።

በተለያዩ የውይይት መድረኮች ከመንግስት አመራሮች ጋር ባደረጉት ግንኙነት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ የወደሙ መኖሪያዎች እንዲገነቡ እና የኦጎሌ ትምህርት ቤት ለትምህርት ክፍት እንዲሆን ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ከመንግስት በኩል የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑ ተገልጿል።

​በሌላ በኩል በዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ በህዝብ ተነሳሽነትና በላብ እንብርት የተገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዳይጀምር በመንግስት አካላት መታገዱ ከፍተኛ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቅሬታ አስከትሏል።

​በ2016 ዓ.ም በአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የገንዘብ፣ የጉልበት እና የቁሳቁስ አስተዋጽኦ መገንባት የጀመረው ይህ ትምህርት ቤት፣ አስፈላጊ ማቴሪያሎች ተሟልተውለት በ2017 ዓ.ም ለአገልግሎት የበቃ ቢሆንም የጋሞ ዞን እና የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ መንግስት አካላት ከፖለቲካዊ ስልጣን ፍላጎትና ከጸጥታ ስጋት ጋር አያይዘው ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ትምህርት ቤቱ እንዳይከፈት አግደውታል ብሏል።

​በአካባቢው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመከፈቱ ምክንያት፣ ተማሪዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲደርሱ በአቅራቢያቸው መማር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ልጆቻቸውን ወደ አጎራባች ዞኖችና ከተሞች ልከው ማስተማር ያልቻሉ ወላጆች ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ተገደዋል።

ነዋሪዎች እንደሚሉት “ልጆቻችን ለትምህርት ብለው ወደ አጎራባች አካባቢዎች ለመሰደድ ተገደዋል። በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና፣ ለስነ-ልቦና ስብራት እና በተለይም ሴት ተማሪዎች ለከፋ ጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ እየሆኑ ይገኛሉ” ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

​በተመሳሳይ በዘይሴ ዳንብሌ ቀበሌ የሚገኘው የህዝብ ጤና ጣቢያ ከተቋቋመበት ሰብአዊና የህክምና አገልግሎት መስጠት አላማ ውጭ በኃይልና በግዳጅ ለክልሉ የጸጥታ አካላት (አድማ ብተና) ካምፕነት እንዲውል መደረጉ ከፍተኛ ህጋዊና ማህበራዊ ውጥረት ፈጥሯል።

​ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ “ህግ ለማስከበር” በሚል ሰበብ ወደ አካባቢው የገቡት የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የጤና ጣቢያውን በኃይል ተቆጣጥረው ለሶስት ዓመታት ያህል ለወታደራዊ ካምፕነት ሲጠቀሙበት ይገኛሉ።

ይህ ድርጊት ህፃናት፣ ድገተኛ ህመምተኞች እንዲሁም እንደ ደም ብዛት፣ ስኳርና ኤች.አይ.ቪ ያሉ ስር የሰደዱ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች መደበኛ ክትትልና ህክምና እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።

​የአካባቢው ነዋሪ አቶ ገብሬ ኦንቶሎ እንደገለጹት “የጸጥታ ኃይሉ የጤና ተቋሙን ከተቆጣጠረ ወዲህ መደበኛ የህክምና አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ቆሟል። የጤና ባለሙያዎችም ከስራ ቦታቸው በመፈናቀላቸው ምክንያት ህዝቡ ለከፍተኛ ሰብአዊ ውድቀት ተዳርጓል።

በተለይም ወላድ እናቶች በአቅራቢያቸው ህክምና በማጣታቸው በቤት ውስጥ ለመውለድ ተገደዋል፤ በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ደም መፍሰስ ለሞትና ለከባድ የጤና ጉዳት እየተጋለጡ ይገኛሉ” ብለዋል።

የህክምና ተቋማት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግ እና በሀገር ውስጥ ህጎች ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው በመሆናቸው፣ ለወታደራዊ ተግባር መዋላቸው የማህበረሰቡን መሰረታዊ የህይወት አድን መብት የሚጥስ መሆኑን ታዛቢዎች ያስረዳሉ።
​
​ሁሉንም ሀሳብ በጉዳዩ ዙሪያ ለ WT Media አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች እንደገለጹት ምንም እንኳን የህዝቡ የመዋቅር ጥያቄ በህገ-መንግስቱ መሰረት እስካሁን ምላሽ ባያገኝም፣ የቀድሞ የደቡብ ክልል ፕረዚዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ በመስከረም 22 ቀን 2019 ዓ.ም ተክተው ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶክተር) ከመጡ ወዲህ ከዚህ ቀደም በዘይሴ የነበረው ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ማሳደድ እና እስራት በአካባቢው መቀነሱንና መቆሙን መስክረዋል።

ይህም በአካባቢው አንጻራዊ ሰላምና ተስፋ እንዲፈጠር አድርጓል።

​አዲሱ አመራር ነገሮችን በኃይል ከመጫን ይልቅ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያሳየ ያለው በጎ ፍላጎት ትልቅ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑን የአከባቢው ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከሁለት ቀን በፊት ከኮንሶ፣ ከኧሌ፣ ከኮሬ፣ ከቡርጂ እና ጋርዱላ ዞን ከተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በነበራቸው ውይይት እንደተናገሩት ​”የውስጥ ሰላም በኃይል ሊጠበቅ አይችልም፤ ሰላም ሊገኝ የሚችለው በመግባባት ነው። ‘ለእኔ ብቻ’ የሚል አስተሳሰብ የግጭት መነሻ እንጂ ሰላምን አያመጣም፤ የውስጥ ሰላምን ለማስጠበቅ የምንችለው በመስጠት እና በመቀበል መርህ ነው” ሲሉ የህዝብ ጥያቄዎችን ከጉልበት ይልቅ በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶክተር)

​ይህ የአዲሱ አመራር የሰላም ጥረትና የውይይት አቅጣጫ የሚናቅ ባይሆንም፣ በዘይሴ አካባቢ የተጋረጠውን ሰብአዊ ቀውስ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት ግን መንግስት በተግባር የተፈናቀሉ ዜጎችን በአስቸኳይ ማቋቋም፣ የወታደራዊ ኃይሎችን ከጤና ጣቢያው ማስወጣት እና የታገዱ ትምህርት ቤቶች ለህፃናት ክፍት እንዲሆኑ የማድረግ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት ሲሉ የአከባቢው ነዋሪዎቹ ተማፅነዋል።

​WT Media በቀጣይም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ አጠቃላይ ሁኔታዎችን የቀድሞውንና የአሁኑን ልማት፣ ሰላም፣ ጸጥታ፣ መንግስታዊ አሰራር እና ፍትህ በመቃኘት ጥልቅ የምርመራ ዘገባዎችን በመስራት ለአድማጭ ለተመልካቹ የሚያደርስ ይሆናል።

​ WT Media | Voice of Marginalized Community