ከጋሞ ዶርዜኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ማብራሪያ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከዚህ ቀደም በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል «በጋሞ-ዶርዜ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሊጀመር ነው» በሚል ርእስ ያጋራውን መረጃ ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች የቀረቡትን የማበረታቻ፣ የድጋፍ፣ የጥያቄ፣ የቅሬታና የነቀፋ አስተያየቶች በአክብሮትና በትኩረት መቀበሉን ገልጾ በጉዳዩ ላይ አጠቃላይ ማብራሪያና ማስተካከያ አውጥቷል።
ማኅበሩ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ «ጋሞ-ዶርዜ» የሚለውን አጠራር የተጠቀመው አዲስ ቋንቋ ለመፍጠር፣ የማንንም ማንነት ለመቀየር ወይም የተለየ ማኅበረሰብ ማንነትን ለመወሰን በማሰብ እንዳልሆነ አስረድቷል።
አጠራሩ በሰፈረው መሠረት ጋሞኛን በቋንቋ ደረጃ፣ በዘዬ (ዳያሌክት) ደረጃ ደግሞ ዶርዜኛን በማመልከት ሁለቱን ስሞች በአንድነት የመጥራት አሠራር የተከተለ መሆኑን እና ዓላማውም የታሰበውን የቋንቋ ዘርፍና የተጠቃሚውን ማኅበረሰብ ለማመላከት ብቻ እንደነበር ገልጿል።

ይሁን እንጂ ይህ አጠራር በቂ ማብራሪያ ሳይሰጥ መቅረቱ ለግራ መጋባትና ለቅሬታ መንስኤ መሆኑን በመገንዘብ፣ የታቀደው የትርጉም ሥራ መጠሪያ «በጋሞ ቋንቋ በዶርዜኛ ዘዬ (ዳያሌክት) የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ፕሮጀክት» በሚል ግልጽ አገላለጽ እንዲስተካከል አድርጓል።
ማኅበሩ በመግለጫው እንዳብራራው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ዋና ዓላማ የመጀመሪያውን መልእክት በትክክል፣ በግልጽነትና ለተቀባዩ ማኅበረሰብ ተፈጥሯዊ በሆነ አገላለጽ ማስተላለፍ ነው። የዘዬ ልዩነቶች የመልእክቱን ግንዛቤ በሚጎዱበት ወይንም በሚቀይሩበት ሁኔታ፣ በተገቢው የቋንቋና የትርጉም ጥናት ላይ ተመሥርቶ ለተለየ ዘዬ የትርጉም ሥራ ማከናወን የተለመደና ተገቢ አሠራር መሆኑን ጠቁሟል።
ይህም አሠራር ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች ቋንቋዎች መከናወኑን አንስቷል።
ለአብነትም በኦሮምኛ፦ በአርሲ ዘዬ፣ በጉጂ ዘዬ እና በምሥራቅ ኦሮምኛ ዘዬ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራዎች ተከናውነዋል።
በጉሙዝኛ፦ በደቡብ ጉሙዝና በሰሜን ጉሙዝ ዘዬዎች የትርጉም ሥራዎች ተከናውነዋል፤ አሁንም በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በጉራጌኛ፦ በቸሃ፣ በቀቤና፣ በመስቃንና በክስታኔ ዘዬዎች የተሠሩ የትርጉም ሥራዎች ተጠቀሰዋል።
በተለያዩ ዘዬዎች ትርጉም ማዘጋጀት ማኅበረሰብን ለመከፋፈል ወይም ድብቅ ዓላማ ለማራመድ የሚከናወን ሳይሆን ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሚያውቁትና በሚጠቀሙበት አገላለጽ እንዲረዱና በሕይወታቸው እንዲተገብሩ ማገዝ ብቻ መሆኑን ማኅበሩ በአጽንኦት ገልጿል።
ለአንድ መቶ ዓመት የሚጠጋ የአገልግሎት ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ የእግዚአብሔር ቃል በቋንቋ ልዩነት ምክንያት ለማንም እንግዳ እንዳይሆን በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ አረጋግጧል።
በዶርዜኛ ቋንቋ እንዲዘጋጅ የታቀደው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምም የዚሁ ተልእኮ አካል መሆኑን ገልጾ፣ ማኅበረሰቦችን በቅንነት አስተያየታቸውን ለካፈሉ አካላት ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ዓላማ ሰዎችን መለያየት ሳይሆን ሁሉም የእግዚአብሔርን ቃል በሚረዳበት ቋንቋ እንዲያገኝ ማድረግ መሆኑን በማስታወስ፣ የጋራ ተልእኮውን በመግባባት፣ በመከባበርና በትብብር እንዲያሳካ ጥሪ አቅርቧል።
መጽሐፍ ቅዱስ በየቋንቋው እና በየዘዬው መተረጎሙ ያለው ፋይዳና የተቃውሞው ምስጢር በተመለከተ ቋንቋን እና አከባቢውን በደምብ የሚያውቁት አቶ አይናለም ታደሴ በሰጡት አስተያየት በጋሞ ዞን ከሚነገሩ ቋንቋዎች/ዘዬዎች መካከል በአንዱ (በዶርዜኛ) የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ መጀመርን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞና አጸፋዊ ማብራሪያ፣ በቋንቋዎች ዕድገት እና በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ታሪክ ዙሪያ በርካታ መሞገቻዎችን የሚያስነሳ ነው።
እንደ እሳቸው ገለፃ በታሪክ እንደምናየው በርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንዲያድጉ፣ ሰዋስው እንዲበጅላቸውና ዘመናዊ የጽሑፍ ቅርጽ እንዲይዙ የጎላ ሚና የተጫወተው የሚሲዮናውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ነው። ለአብነት ያህል፣ የአባ ገብረኤቭ (አባ አናሲሞስ ነሲብ) የኦሮምኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለኦሮምኛ ቋንቋ ሥነ-ጽሑፍ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ ወደር የለውም።
በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ የሀገራችን ክፍሎች (በጋሞ፣ በጎፋ እና በዳውሮ አካባቢዎች) የወላይትኛ ቋንቋ እጅግ እንዲስፋፋና እንደ የጋራ መግባቢያ እንዲያገለግል ያደረገው አብይ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ በወላይትኛ መተርጎሙ እና የስብከት እንዲሁም የዝማሬ አገልግሎት በዚሁ ቋንቋ በመከናወኑ ነበር።
”መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ ብቸኛ መጽሐፍ ነው” እንደሚባለው ሁሉ፣ በጋሞ ዞን ውስጥም በርካታ የራሳቸው ልዩ ባህርይ ያላቸው አነጋገሮችና ቋንቋዎች ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል እንደ ባልታ፣ ሻራ፣ ዛርጉላ እና ጋንታ ያሉ ቋንቋዎች ወይም የንግግር ዘይቤዎች ከሌሎች የአካባቢው አነጋገሮች ጋር ሲነፃፀሩ በቀላሉ የመግባባት ዕድል የማይሰጡ፣ በየአካባቢው ባሉ ሕፃናትና አዋቂዎች አፋቸውን የፈቱባቸው መሰረታዊ ቋንቋዎች ናቸው ብለዋል።
ምንም እንኳ የዎላይትኛ፣ የጋሞኛ እና የጎፍኛ መደበኛ ተናጋሪዎች እርስ በእርስ በቀላሉ የመግባባት ዕድል ቢኖራቸውም፣ በየቀበሌው ባሉ ጥቃቅን የዘዬና የቋንቋ ልዩነቶች ምክንያት የመልእክት መራራቅ ይከሰታል። ለምሳሌ የቦንኬ ልጅ “Aso” ሲል የባልታ ልጅ “Gero?” የሚልበት አገላለጽ የሚያሳየው፣ መደበኛው የቋንቋ ሥርዓት ለአንድ አካባቢ አነጋገር የሚያደላ በመሆኑ፣ የሌላው አካባቢ ሕፃናት መደበኛውን ቋንቋ በሂደት ለመማር እንደሚገደዱ ነው።
ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና የምሥረታ ዓላማ የእግዚአብሔርን ቃልና የምስራቹን መልእክት በሰው ልጆች አፍ መፍቻ ቋንቋ ማድረስ እንጂ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ባለመሆኑ መጽሐፉ ለሰዎች በቀለለና በሚረዱት ቋንቋ ወይም ዘዬ ተተርጉሞ መቅረቡ የሚጎዳው አካል አይኖርም።
እንዲያውም በየዘዬውም ቢሆን የሚለያይና የሚናገር ማኅበረሰብ እስካለ ድረስ ቃሉ በዚያው ዘዬ መጻፉ ሕዝቡን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ ጉዳት የሚያስከትል አይደለም። በጋሞ፣ በጎፋና በዎላይታ ዞኖች በሚነገሩ ሁሉም ዘዬዎችና ቋንቋዎች መጽሐፉ ቢተረጎም ለአካባቢው ሥነ-ጽሑፍና ማኅበራዊ ዕድገት ትልቅ ዕድል የሚከፍት እንጂ የሚያሳስብ ጉዳይ ሊሆን አይገባም” የሚል ሀሳብ አጋርተዋል።
WT Media | Voice of Marginalized Community