በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ «አርባ ክላላ» በተባለ ስፍራ በተፈጸመ ጥቃት የአምስት ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል። ከሟቾቹ መካከል አንዱ ነዋሪ በሕይወት ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉ ተረጋግጧል።

እንደ አካባቢው ነዋሪዎችና ምንጮች ዘገባ ከሆነ፣ ጥቃቱ ከኧሌ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የተፈጸመ ሲሆን፣ በቀጠናው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣው አለመረጋጋት አካል እንደሆነ ተጠቅሷል።
በኮልሜ ወረዳና በአካባቢው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የተቀሰቀሱት ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎችን ለአደጋ ማጋለጣቸውና የመኖሪያ መንደሮች መቃጠላቸው ይታወቃል። ለአብነትም፦
ከወር በፊት ታጣቂዎች በወረዳው ባካሄዱት ወረራ የሰው ሕይወት ማለፉና በርካታ የመኖሪያ ቤቶች በእሳት መውደማቸው ተዘግቧል።

በአርባ ክላላ አራት ሰዎች ወዲያውኑ ሲገደሉ፣ አምስተኛው ነዋሪ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ ማለፉ ተረጋግጧል።
እነዚህ ተከታታይ ጥቃቶች በወረዳው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የደህንነት ስጋትና የእለት ተእለት ጭንቀት ፈጥረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ ጥቅምት 18 ቀን 2019 ዓ.ም. በካራት ከተማ ከኮንሶ፣ ኧሌ፣ ኮሬ፣ ቡርጂ እና ጋርዱላ ዞኖች ተወካዮች ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ በወሰን አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀው ነበር።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ከግጭት ትርፍ የሚያበቅሉ አካላትን ወደ ሰላም ለማስገባትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸው ነበር።
ሆኖም የኮልሜ ወረዳ ሕዝብና የማህበረሰብ ተወካዮች የተሰጡ የሰላም ቃሎች በተግባር ላይ ውለው አስተማማኝ ደህንነት እንዲረጋገጥላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የአካባቢው ነዋሪዎችና ጥቃቱን ያወገዙ ወገኖች ለክልሉ መንግሥት የሚከተሉትን ዋና ዋና ጥያቄዎች አቅርበዋል።

በኮልሜ ወረዳ በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ አስቸኳይና ገለልተኛ ምርመራ ተካሂዶ ተሳታፊ ታጣቂዎች በሕግ እንዲጠየቁ፤
ታጣቂዎችን በመደገፍና ግጭት በማቀጣጠል በኧሌ ዞን አመራሮች ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችና ክሶች በገለልተኛ አካል ተጣርተው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቀጠናው በበቂ ሁኔታ ተሰማርተው የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወትና ንብረት የማስጠበቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ።
በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን የተመኙት የአካባቢው ተወካዮች፣ ችግሩ በዘላቂነት እስካልተፈታ ድረስ በዞኖች መካከል ያለው ወንድማማችነትና የህዝቦች አብሮ መኖር አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አሳስበዋል።
WT Media | Voice of Marginalized Community