Screenshot_20261104-143113

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ሶዶ ከተማ ሐሰተኛ የግዥ እና የአልጋ ደረሰኞችን በማዘጋጀት ወንጀል የተሰማሩ ሶስት ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ውስጥ ውለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ አድርጎ ባካሄደው ጥናትና ድንገተኛ ኦፕሬሽን ሀሰተኛ ደረሰኞችን በማዘጋጀትና በማቀባበል ወንጀል የተሰማሩ ሶስት ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በከተማው በሚገኝ አንድ ማተሚያ ቤት ውስጥ ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ የወጡ ደረሰኞችን እና አታችመንቶችን በሀሰተኛ መንገድ በማዘጋጀት እና ለተለያዩ አካላት በመሸጥ የታክስ ማጭበርበር ወንጀል እንዲፈፀምባቸው ሲያደርጉ ቆይቷል፡፡

በተደረገው ድንገተኛ ኦፕሬሽን የማተሚያ ቤቱ ባለቤት፣ ፀሀፊ እና ሀሰተኛ ደረሰኞችን በመደለልና በማቀባበል ወንጀል የተሰማራ አንድ ግለሰብ በህግ ቁጥጥር ውስጥ ውለው ምርመራው እየተጣራ ይገኛል፡፡

በዎላይታ ሶዶ ከተማ ገቢዎች መምሪያ ስም የተዘጋጁ ማህተሞች እና ቲተሮች፣ ሀሰተኛ የታክስ ክሊራንሶች፣ የፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የገቢ ደረሰኞች፣ የወጪ መጋራት ማስረጃዎች፣ የቀድሞ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ፋይናንስ ቢሮ ያሳተማቸው የእርሻ ሥራ እና የአፈር ማደበሪያ ገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኞች፣ የማዘጋጃ ቤት ማህተሞች፣ የህጋዊ ግብር ከፋዮችን ስምና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የያዙ ሀሰተኛ ደረሰኞች እንዲሁም በነዚህ የተዘጋጁ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶች በማተሚያ ቤቱ በተደረገ ፍተሸ ተገኝተዋል ብሏል፡፡

ሀሰተኛ የግዥ እና የአልጋ ደረሰኞችን በማዘጋጀት እንዲሁም ተቀብሎ ህጋዊ አስመስሎ በመጠቀም የታክስ ስወራና ማጭበርበር ወንጀል በሚፈፅሙ አካላት ላይ ቢሮው ከመቼውም ጊዜ በተለየ ክትትልና ፍተሻ በማድረግ እንዲሁም በጥናት ላይ የተመሰረተ ድንገተኛ ኦፕሬሽን በማካሄድ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረቡን ተግባር አጠናክሮ እንዲሚቀጥል በሚል ቢሮው አሳስቧል፡፡