በኦሮሚያ ክልል የቀድሞ አርሲ ዞን በአዲሱ አደረጃጀት ደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ሲርካ ወረዳ ቢርቦና ጮሌ ቀበሌ ጥቅምት 14 ቀን 2019 ዓ.ም ኦነግ ሸኔ እና በአካባቢው የታጠቁ ኢመደበኛ ግለሰቦች ፈፀሙት በተባለ ጥቃት፣ የቀበሌ የፀጥታ አካላትን፣ ሚሊሺያዎችን እና ሰላማዊ ሰዎች ጨምሮ 48 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አደርጓል።
ኮሚሽኑ በአከባቢው ታጥቆ የሚቀሳቀሰው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራ ያለው ኦነግ ሸኔ ወደ ቀበሌው በአራት አቅጣጫ በመግባት በፈጸመው ጥቃት 23 በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ ጸጥታ አካላት፥ 5 የሚሊሻ አባላት እንዲሁም 13 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ዘርዝሯል።
በተመሳሳይ በአካባቢው የታጠቁና ኢ-መደበኛ ባላቸው ግለሰቦች ሰባት ሲቪል ሰዎች የተገደለ መሆኑን የጠቀሰው ኢሰመኮ በዕለቱ በጠቅላላው 48 ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።
በዚሁ በኦነግ ሸኔ ፈጸመው በተባለው ጥቃት ከደረሰው ሞት በተጨማሪ በ20 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት፤ 21 መኖሪያ ቤቶች መቃጠል፣ 247 ቤተሰቦች ከአካባቢው መፈናቀል፣ ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልተለየ የቀንድና የጋማ ከብቶች ተዘርፈዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥት ጉዳቱ ተደጋግሞ የደረሰበት አካባቢ ያለውን የጸጥታ አካላት አደረጃጀት እንዲገመግምና እንዲያስተካክል፣ ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ዘላቂ የመከላከል ርምጃዎችን እንዲወስድ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትም እንዲዘረጋ እና ዜጎችን የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል። ጉዳቱንም ምርምሮ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ምርምር ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምሥራቅ ዞን አርሲ ሲርካ ወረዳ በታጣቂዎች በተፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች እና የጸጥታ አካላት ሕይወት ማለፉ፣ ንብረት መውደሙና ዜጎች መፈናቀላቸው የጸጥታው መዋቅር ያለውን ተጋላጭነት በግልጽ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዳስገነዘበው፣ መንግሥት ተደጋጋሚ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የጸጥታ አደረጃጀቱን ሊገመግም፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ሊዘረጋ እና የዜጎችን ደህንነት በዘላቂነት ሊያስጠብቅ ይገባል። እንዲሁም በድርጊቱ ላይ አጠቃላይ ምርመራ ተካሂዶ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስቧል።