«ሆፕ ፎር ጃስቲስ» (Hope for Justice) የተባለ ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን ስር ባሉ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን ከብዝበዛ ለመጠበቅ የሚያስችል ትልቅ የሁለት ዓመት ፕሮጀክት እንደሚጀምር በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል። ፕሮጀክቱ የህጻናትን ለብዝበዛ ተጋላጭ የሚያደርጉ ዋና ዋና ስር ነቀል ምክንያቶችን በመቅረፍ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል ያለመ ነው ብሏል።
እስከ መጋቢት 2028 ዓ.ም. ድረስ የሚቆየው ይሄው ፕሮጀክት፤ ሴቶችን ማብቃት፣ የማህበረሰብ ጥበቃ ስርዓቶችን ማጠናከር እና በፀረ-ሰዎች ዝውውር ስራዎች ላይ የአካባቢውን ባለቤትነት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ድርጅቱ አስታውቋል።
በፕሮጀክቱ ማዕቀፍ ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉ አዲስ የራስ-አገዝ ቡድኖች (Self-Help Groups) የሚቋቋሙ ሲሆን ይህም ወደ 2,000 የሚደርሱ ሴቶች ገንዘብን እንዲያጠራቅሙ፣ ንግድ እንዲጀምሩ እና የቤተሰባቸውን ገቢ እንዲያሳድጉ ድጋፍ ያደርጋል ብሏል።
የተሻሻለ የቤተሰብ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እና የትምህርት ቤት ቆይታን በማረጋገጥ በግምት 8,000 የሚጠጉ ህጻናት ከዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል በሚል ድርጅቱ በወጣው ማብራሪያ ጠቁሟል።
የአካባቢው ቡድኖች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶች ተወካዮች እና የህጻናት መብት ኮሚቴዎች የህገወጥ ህፃናት ዝውውር ስጋቶችን እንዲለዩ፣ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ እና የተጋለጡ ህጻናትን በተሻለ ሁኔታ እንዲጠብቁ የአካባቢው ቡድኖች ስልጠና ያገኛሉ ሲልም ድርጅቱ አብራርቷል።
የ«ሆፕ ፎር ጃስቲስ ኢትዮጵያ» የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር ሶስና ይርጋ፤ «በስድስት አዳዲስ ወረዳዎች ውስጥ የህጻናትን ብዝበዛ ለመከላከል ይህንን ወሳኝ ስራ በመጀመራችን በጣም ደስተኞች ነን። ዓላማችን የፀረ-ሰዎች ዝውውር ጥረቶች ከማህበረሰቡ የውስጥ አውታረ መረቦች ጋር እንዲዋሃዱ እና ፕሮጀክቱ ካለቀ በኋላም ዘልቀው እንዲቀጥሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መስራት ነው» ብለዋል።

የሆፕ ፎር ጃስቲስ (Hope for Justice) በዎላይታ ዞን ስር ባሉ ስድስት ወረዳዎች የጀመረው ይህ አዲስ ፕሮጀክት የህጻናትን ብዝበዛና ሕገ-ወጥ ዝውውር ለመከላከል ከምንጩ የሚሰራ ትልቅ ምዕራፍ ነው። ፕሮጀክቱ ሴቶችን በኢኮኖሚ በማብቃት፣ የቤተሰብን ገቢ በማሳደግ እና የህጻናትን የትምህርት ቤት ቆይታ አስተማማኝ ከማድረግ ባለፈ፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የወጣቶች ተወካዮች በማስተማር ዘላቂ መፍትሄዎችን ለመዘርጋት ያለመ ነው። በርካቶች ለህገወጥ ሰዎች ዝውውር እና ጉልበት ብዝበዛ የሚዳረጉበት በዚህ በዎላይታ አከባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን እና ህጻናትን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ ስራ፣ ማህበረሰቡ ራሱ የፀረ-ብዝበዛ ዘመቻው ባለቤት እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
WT Media | Voice of Marginalized Community