የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበጀት፣ የመዋቅር እና የሀብት አስተዳደር ችግሮች አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚፈልጉ ተገለፀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተካሄደውን ወቅታዊ ክልላዊ የምክክር መድረክ እና የትኩረት አቅጣጫዎችን መሠረት በማድረግ፤ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች (ለአብነትም በዎላይታ ዞን አስተዳደር ሰፊ ግምገማ የተደረገባቸውን ጉዳዮች ጨምሮ) ያለው ከባድ የበጀት እጥረት፣ የመዋቅር አላግባብ ማስፋፋት እና የሀብት አስተዳደር ችግሮች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

በክልል ፋይናንስ ቢሮ መሪነት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ሰሞኑን በተካሄደው የበጀት እና የገቢ አስተዳደር የምክክር መድረክ ላይ በክልሉ የሚገኙ መዋቅሮች የበጀት ውሱንነት፣ ሕገ-ወጥ ቅጥሮች እና የሀብት አጠቃቀም ብቃት ማነስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በሰፊው ተገምግሟል።

በቢሮው የተወሰዱ ጥብቅ የመቆጠብ እና የቁጥጥር «ቀይ መስመሮችም» ይፋ ሆኗል። 

በመድረኩ ላይ በዝርዝር ለአብነት እንደተገለጸው በዎላይታ ዞን ማዕከልን ጨምሮ አጠቃላይ 27 መዋቅሮች የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ መዋቅሮች የሰራተኞቻቸውን ወርሃዊ ደሞዝ ሙሉ በሙሉ ለመክፈል የማይችሉበት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

ከጠቅላላው መዋቅሮች ውስጥ 17 የሚሆኑት ሙሉ ደሞዝ መክፈል የማይችሉ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም 7 መዋቅሮች የ10 ወር፣ 6 መዋቅሮች የስምንት ወር፣ እንዲሁም 4 መዋቅሮች የ6 ወር ደሞዝ ብቻ መክፈል የሚችሉበት አቅም ላይ ወርደዋል ሲሉ የዞኑ ምክትል አስተዳደሪና የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ ታምራት ታንጋ (እጩ ዶክተር) አብራርተዋል።

በመድረኩ እንደገለፀው ችግሩ የሀብት እጥረት ብቻ ሳይሆን የሀብት የማስተዳደር ብቃት ማነስ ውጤት ነው። አሁን ያለው አካሄድ ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በህሊና ዳኝነት ሊታረም እንደሚገባ ተመላክቷል።

የዞኑን ማዕከል ሳያውቁ እና ፈቃድ ሳይጠይቁ የሚደረጉ ሕገ-ወጥ ቅጥሮች እና ከመጠን በላይ የተስፋፉ መዋቅሮች ለбጀት ቀውሱ መባባስ ዋና ምክንያት መሆናቸው ተነግሯል።

ለአብነትም የዞኑን ማዕከል ሳያውቁ ከ60 እስከ 78 የሚደርሱ ሰዎችን የቆጠሩ እና የቀጠሩ መዋቅሮች መኖራቸው ታውቋል።

በወር ከ500 ብር በላይ ገቢ የማይሰበስብ ማዘጋጃ ቤት፤ እስከ 22 ሰራተኞችን ቀጥሮ ለማስተዳደር በመሞከሩ ለኪሳራ መዳረጉ የሀብት አስተዳደር ብቃቱ ክፉኛ መውረዱን እንደ ማሳያ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተውልደ ተስፋዬ አስረድተዋል።

ወጪ በጀት ሊመራ እንጂ በጀት በወጪ ሊመራ እንደማይገባ ጠቅሶ አሁን ያለው አሰራር በህሊና ዳኝነት ሊታረም እንደሚገባ ተጠቁሟል። 

ይህንን አስቸኳይ ችግር ለመቋቋም ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ሊወሰዱ የሚገቡ ጥብቅ እርምጃዎች ተቀምጠዋል።

እንደ ባህላዊ ልብስ ግዥዎች፣ የጃኬት፣ ስካርብ፣ መስተንግዶ፣ የሥልጠና ወጪዎች እና የአበል ክፍያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጎ እስከሚቀጥለው ጊዜ ድረስ እንዲቆሙ ውሳኔ ተላልፏል። 

«ጉዛ የመልበስ አቅም እንቀንስ ማለታችን ላልፈልግ ሳይሆን፣ አሁን ካለው የችግር አውድ አንጻር ማስቆም ያለብንን ማስቆም ስላለብን ነው» ተብሏል።

ክልሉን አሁን የገጠመው የበጀት ውሱንነት እና የደሞዝ ክፍያ አቅም ማነስ ችግር የሀብት እጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ-ወጥ ቅጥሮችና የአስተዳደር ብቃት ማነስ ውጤት መሆኑ በግልጽ ታይቷል።

 በመድረኩ ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ወጪዎችና ቅጥሮች በጥብቅ ቁጥጥር ሊመሩ እንደሚገባና ተቋማትና ኃላፊዎችም ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን በብቃትና በቁጠባ መንፈስ በመወጣት፣ ሕዝብን በሚጎዳ መልኩ የሚደረጉ ብክነቶችን በአፋጣኝ ሊቆሙ ይገባል በሚል ስምምነት ተጠናቋል።