1000160551

በኦሮሚያ ክልል፤ በቀድሞው ምሥራቅ አርሲ ዞን በአሁኑ ደቡብ ምሥራቅ ዞን ሮቤ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት ያልታጠቁ ንጹሐንን ህፃናትን ጨምሮ ሚሊሻ እና የፖሊስ አባላት ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

​የሟቾችን አስከሬን መቁጠራቸው የገለጹ የአይን እማኝ ካህን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል “በእንደቶ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት የ34 ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል” ብለዋል። ብዙሃኑ ሚሊሻና የፖሊስ አባላት እንደሆኑ ገልጸዋል።

​”የ34 ሰዎችን አስከሬን ሰብስበን ነበር። ከእነዚህ ውስጥ የእንደቶ ቀበሌ ነዋሪ ያልሆኑ ለግዳጅ የመጡ የ9 ሰዎችን አስከሬን ቤተ ክርስቲያን አሳድረን በሕግ አካላት ወደ አካባቢያቸው እንዲመለስ አድርገን ተቀብረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

​”25 ሟቾች እንደቶ ማርያም ተቀብረዋል” ያሉት እኚሁ ቤተክርስቲያን አገልጋይ፣ ሌሎች የቆሰሉ 4 ሰዎች ወደ ህክምና እየሄዱ በነበረበት አንዱ መንገድ ላይ ሕይወቱ አልፎ በወረዳው ሰዲቃ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን መቀበሩን ገልጸዋል።

​ከሟቾች መካከል ያልታጠቁ ምን ያህል እንደሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ህፃናት ጭምር እንዳሉበትና ቁጥራቸው ከ7 በላይ እንደሆነ አስረድተዋል።

​እኚሁ እማኝ፣ መጀመሪያ ጥቃት የተከፈተው በእንደቶ “ቂሊሳ ደምበል” ሃይስኩል ፣ “ቃኮ አደጀቦ” ባሉ ካምፖች ፣ በከተማው ባለ አንድ ካምፕ መሆኑን ገልጸዋል።

​ጥቃት አድራሽ ታጣቂዎች አካባቢውን ሲጠብቁ በነበሩ ሚሊሻና የፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተናግረዋል።

​”ቀጥታ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን የሕግ አካላትና ሚሊሻውን ለማጥቃት ሚሊሻዎችና ካምፕ የሚጠብቁት ላይ ነው ጥቃት የከፈቱት፤ ሚሊሻዎቹ ምሽግ ሰርተው ማህበረሰቡን በሚጠብቁበት ነው ጥቃት የተከፈተባቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

​”ታጣቂዎቹ በ3ቱ ካምፖች ጠዋት ንጋት 11 ሰዓት ገደማ ከበባ አደረጉ፤ ሚሊሻዎቹ ህዝብ ሲጠብቁ አድረው 11 ሰዓት ነው የሚተኙት። ታጣቂዎቹም አጥንተው ብዙ ሰዎች ጨረሱ” ብለዋል።

​የፖሊስ አባላትም ህይወታቸውን እንዳጡም ጠቁመዋል።

​ጥቃት ከከፈቱት ታጣቂዎችም የተገደሉ እንዳሉ ገልጸው “የጥቃት አድራሾቹ አባላት ሲገደሉ ወዲያው አስከሬን እየተሸከሙ ነው የሚሄዱት፤ ቁጥራቸው አይታወቅም” ብለዋል።

​እኚሁ ቃላቸውን የሰጡ እማኝ “ታጣቂዎቹ የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” ብለው “ንጹሐን ገድለዋል፤ ሱቆች ሰባብረዋል፤ ንብረት ዘርፈዋል። ብዙ ጥቃት አድርሰዋል። ከፖሊስና ሚሊሻ ጋር ተታኩሰዋል” ብለዋል።

​አንድ የሮቤ ወረዳ ቤተክህነት አካል፣ “የምናውቃቸው ንጹሐን ሞተዋል። አንድ የጓደኛችን ጓደኛ ልጅ፤ አንድ የካህን የልጅ ልጅ ተገድለዋል። እኔ ራሱ ያልታጠቁ ወደ 4 ንጹሐን ሰዎች መገደላቸውን አውቃለሁ። እነዚህ እኔ የማውቃቸው ብቻ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

​”‘የ25 ሰዎችን አስከሬን ቀብረናል። የዘጠኙ አስከሬን ወደ ትውልድ ቦታቸው ተሸኝቷል። 25ቱ በአንድ ቦታ ቀብረናል'” የሚል መረጃ ከእንቀቶ እንደደረሳቸው ገልጸዋል።

ቲክቫ ኢትዮጵያ ​ያነጋገረው አንድ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ፣ “እንደቶ ላይ የተገደሉት ከ40 በላይ ሰዎች ናቸው። ትልቁን ቁጥር የሚይዘው ሚሊሻ ነው። የእንደቶ ማርያም ቤተክርስቲያን በር ተመቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

​”እንደቶ ቀበሌ 12 ልጆች ትላንት ተመተው ከባድ ህመም ላይ ናቸው፤ በህክምና እጦት ምክንያት መንገድ ዝግ ነው ድምጽ ሆኗቸው” በማለት ጠይቀዋል።

​እኚሁ ነዋሪ በሰጡን ገለጻ፣ ከጥቃት አድራሾቹ ታጣቂዎችም እንደሞቱ ገልጸዋል።

​የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ልውውጡ “ሚሊሻና ጥቂት ራሳቸውን ለመከላከል የሰለጠኑ ገበሬዎች” በአንድ በኩል፣ ጥቃት አድራሽ ታጣቂዎች በሌላ በኩል መሆኑን አስረድተዋል።

​አንድ የዞኑ ሀገረ ስብከት አመራር በሰጡን ቃል፣ የሟቾች ብዛት ከ40 እንደሚበልጥ ገልጸው፣ “ሚሊሻዎችም ተገድለዋል።

መጀመሪያ ሚሊሻዎቹን ከመቱ በኋላ ነው ቀጥለው ወደ ህዝቡ የሄዱት” ብለዋል።

​በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት የመሪ እቅድ መምሪያ ኃላፊ መጋቢ ሰላም ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

​”በሮቤ ወረዳ በተለይ ትናንት ነው ግድያው የበረታው፤ እንደቶ እና ሰዲቃ ቀበሌ ላይ የሟቾች ቀብር ተፈጽሟል። በአጠቃላይ ወደ 40 የሚደርሱ ሰዎች ቀብር ተፈጽሟል፤ አብዛኛዎቹ ሟቾች ምዕመናን ናቸው፤ ጥቃቱን ለመከላከል የተሰማሩ ሚሊሻዎችም ተገድለዋል” ብለዋል።

​ኃላፊው “አጥቂዎችን የሚከላከሉ የጸጥታ አካላት የጥቃቱ ሰላባ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው” ያሉ ሲሆን “እንደ አርሲ ስንመለከት ይሄ ጥቃት ደርሶ ትናንት የተጀመረ አይደለም፤ ብዙ አመታት የዘለቀ ጥቃት ነው” ብለዋል።

​”ኢላማ ያደረገው ምዕመኑን ነው” ያሉት መጋቢ ሰላም ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ “ይህ የምንደብቀው ነገር አይደለም” ብለዋል።

አክለው “በአካባቢው ህብረተሰቡን ለመጠበቅ የተቀመጡ የጸጥታ አካላት አሉ፤ ጥቃት አድራሹ ታጣቂ እነዚህን ካጠቃ በኋላ ነው ወደ ህብረተሰቡ የሚገባው” ሲሉ አስረድተዋል።

​”ጥቃቱ ማቆሚያ አጥቷል፤ ጥቁር ጠባሳ የጣለ ነው” ያሉት ኃላፊው፥ “አሁንም አካባቢው ያልተረጋጋ ነው። ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕም ዛሬ በአሰላ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ጥቃቱ እንዲቆም አሳስበዋል” ብለዋል።

​ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ማብራሪያ የጠየቃቸው የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ ዘገባው እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አልሰጡም።

​WT Media | Voice of Marginalized Community