1794856511810

​በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ላይ የምትገኘው ሞያሌ ከተማ ዳግም በከባድ የጦር መሳሪያዎች እሩምታ እየተናወጠች ትገኛለች። ከአንድ ወር ገደማ በባንዲራ መስቀል ውዝግብ ተጀምሮ ከፍተኛ ሰብአዊ ውድመት ሲያስከትል የቆየው ግጭት በዛሬው ዕለት (ህዳር 7 ቀን 2019 ዓ.ም/ November 16/2026 G.C) በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ታጣቂ ኃይሎች መካከል በከባድ መሳሪያ የታገዘ አዲስ እና አውዳሚ ጦርነት መቀስቀሱን የ WT Media የመስክ ምንጮች ከስፍራው አረጋግጠዋል።

​WT Media ቀውሱ ከተጀመረበት የመጀመሪያው ቀን አንስቶ ያለማቋረጥ እየተከታተለ ሲዘግብ የቆየ ሲሆን ከ2 ቀናት በፊት ባወጣነው ጥልቅ የምርመራ ዘገባም በከተማዋ የደረሰውን አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ እና ከ50,000 በላይ ዜጎች ወደ ሰሜን ኬንያ መሰደዳቸውን ይፋ ማድረጋችን ይታወሳል።

አሁን የተቀሰቀሰው አዲስ ጦርነት ግን የተረጋጋ የሚመስለውን የአካባቢውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ወደ ለየለት ቀውስ ከቶታል።
​
​በሞያሌ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል ታጣቂዎች መካከል ከባድ መሳሪያ የታከለበት ቀጥተኛ ውጊያ መቀስቀሱ በነዋሪዎችና በመስክ ሪፖርቶች ቢረጋገጥም የፌዴራል መንግሥት አመራሮች የሚሰጡት መግለጫ ግን ከመሬት ላይ እውነታ ጋር ፍጹም የሚጣረስ ሆኖ ተገኝቷል።

​የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከኤን.ቢ.ሲ (NBC) ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሞያሌውን ግጭት አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰማው ጩኸት ባለፈ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል አስተዳደሮች በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አክለውም «የሁለቱ ክልል ኃይሎች ከባድ መሳሪያ ታጥቀው ገጥመዋል ተብሎ የሚቀርበው ዘገባ የአንዳንድ አካላትን ‘ምኞት’ ከመግለጽ የዘለለ አይደለም» ሲሉ አስረድተዋል።

​ይሁን እንጂ በዛሬው ዕለት ከስፍራው የደረሱን አዳዲስ መረጃዎችና የዓይን እማኞች ምስክርነት በከተማዋ ዳርቻዎች ከባድ መድፎችና የጦር መሳሪያዎች ድምጽ ሲሰማ መዋሉንና የሁለቱ ክልሎች ታጣቂ ኃይሎች ወደ ቀጥተኛ ግጭት መግባታቸውን የመስክ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

​በጉዳዩ ዙሪያ አቋሙን የገለጸው የሶማሌ ፌደራሊስት ፓርቲ በበኩሉ የፌዴራል መንግሥትን ዝምታና ቸልተኝነት በጽኑ ወቅሷል። የፓርቲው ዋና ሰብሳቢ አቶ ዩሱፍ ዘላለም ለአዲስ ማለዳ በሰጡት መግለጫ ከ18 ቀናት በላይ የቆየው የሞያሌ ግጭት ከአስተዳደራዊ ይገባኛል ጥያቄ አልፎ ወደ «ክልል ተኮር ግጭትነት» እና ወደ ሰፊ የጦርነት ቀጣና እያደገ መምጣቱን አስጠንቅቀዋል።

​«ችግሩን በውይይትና በሕጋዊ ሂደት የመፍታት ኃላፊነት የገዢው ፓርቲና የፌዴራል መንግሥት ቢሆንም ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተጨባጭ እርምጃ አለመውሰዱና ዝምታን መምረጡ ቀውሱ እንዲስፋፋ አድርጓል» ብለዋል አቶ ዩሱፍ።

ግጭቱ ወደ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ቀጥተኛ ፍጥጫ ማምራቱ ለሌሎች የውጭ ኃይሎች በሀገሪቱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ወይም ጥቃት ለመፈጸም በር ሊከፍት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
​
​በተያያዘ ዜና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር – የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (OLF-OLA) ከፍተኛ መምሪያ ዛሬ ኖቬምበር 16, 2026 (ህዳር 7, 2019 ዓ.ም) ባወጣው መግለጫ፤ በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (EHRC) ሪፖርቶች ላይ ጠንካራ ትችት ሰንዝሯል።

​መግለጫው በቅርቡ በአርሲ (ሲርካ ወረዳ) የተከሰተውን ጥቃት አስመልክቶ ኮሚሽኑ ህዳር 3 ያወጣውን ሪፖርት ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሲሆን የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት የሚመረምር ተቋም ራሱ የሥርዓቱ አካል መሆኑን ገልጿል።

በተለይም መግለጫው የሞያሌን ቀውስ በማንሳት «በሀገሪቱ በተለያዩ ግንባሮች በንጹሃን ላይ በየዕለቱ ጥቃት እየተፈጸመ ባለበት ወቅት ለምን አርሲ ብቻ ተነጥሎ ይመረመራል? በሞያሌ እየተካሄደ ያለውና ቀጣይነት ያለው ጥቃት ለምን ከኮሚሽኑ ምንም ዓይነት ትኩረት አላገኘም?» ሲል ጠይቋል።

​በተጨማሪም OLA በመግለጫው በአርሲ፣ በወለጋ እና በሞያሌ የሚታዩ ግጭቶች ተነጥለው የሚታዩ ሳይሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ሥልጣኑን ለማቆየት ሲል ሆን ብሎ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶችን በማባባስ ማህበረሰቦችን እርስ በርስ የማጋጨት ስልታዊ የፖለቲካ አካሄድ ውጤቶች መሆናቸውን ወንጅሏል።

​ከላይ የተጠቀሱት የፖለቲካ አመራሮች ክርክርና መግለጫዎች በቀጠሉበት በዚህ ሰዓት፣ በሞያሌ መሬት ላይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ግን ከምንጊዜውም በላይ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል።

​የ WT Media ቀደምት ምርመራ እንዳጋለጠው፤ በሞያሌ ከተማ 90 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ቤት ንብረቱን ጥሎ ተሰዷል።

በተለይም በዋና ዋና ሚዲያዎች ትኩረት ያልተሰጣቸው እና ከደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች (እንደ ዎላይታ፣ ቡርጂ፣ ኮሬ፣ ኮንሶ እና ሌሎች ማህበረሰቦች) ለሥራና ለንግድ ወደ ሞያሌ ሄደው ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች፣ ባልፈጠሩት የፖለቲካ ጦርነት መሃል ተቀርቅረው ንብረታቸው ተዘርፎ ለረሃብና ለስደት ተዳርገዋል።

​ከ50,000 እስከ 60,000 የሚደርሱ ተፈናቃዮች ወደ ኬንያ ማርሳቢት ካውንቲ ተሻግረው ያለ በቂ ምግብ፣ ውሃና ህክምና በክፍት ሰማይ ስር እየተሰቃዩ ባሉበት ወቅት፣ ዛሬ በሞያሌ ዳግም ከባድ ጦርነት መቀስቀሱ የተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ተስፋ ይበልጥ የሚያጨልም እና በአካባቢው የቀሩ ጥቂት ንጹሃንን ህይወት ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ሆኗል።
​
​ዳግም የተቀሰቀሰው ከባድ ውጊያ በአስቸኳይ እንዲቆም የአካባቢው ነዋሪዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ እና የፌዴራል መንግሥትም በመሬት ላይ ያለውን እውነታ በመረዳት ተጨባጭ የሰላምና የጸጥታ ማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንዲሁም ለተፈናቀሉና በከፋ ረሃብ ውስጥ ለሚገኙ ንጹሃን ዜጎች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ በሚል ጥሪ አቅርቧል።