በሀገሪቱ ከተፈፀመው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር አንድ ላይ እንዲካሄድ ተወስኖ በተከሰቱ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ መስከረም 20/2014 ዓ.ም የተራዘመው የደቡብ ምዕራብ ክልል ህዝበ-ውሳኔ የሪፈረንደም ምርጫ ለማስፈፀም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ይታወቃል።
በዚህ አደረጃጀት በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ አስተዳደር ስር ከሚገኙ 55 ብሄረሰቦች ጋር አንድ ላይ የነበሩ ኮንታ ልዩ ወረዳ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች በጋራ አንድ ክልል ለመመስረት በየምክር ቤቶቻቸው በወሰኑት መሠረት ብሄረሰቦች ም/ቤትና ምርጫ ቦርድ ፍቃድ ሰጥተው ምርጫውን ለማከናወን ህዝበ-ውሳኔ ቀን እየተጠበቀ ይገኛል።
ለዚህ ምርጫ ማስፈፀሚያ የሚሆኑ የተለያዩ ቅድመ-ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮንታ ልዩ ወረዳ አመያ ምርጫ ክልል ም/አሰፈፃሚ ወ/ሮ ሙሉ ዝናቡ አብራርተዋል ።
ከፌዴራል ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የምርጫ ማስፈፀሚያ ቁሳቁሶችንና ግብዓት ማምጣታቸውን የተናገሩት ወ/ሮ ሙሉ በልዩ ወረዳው 70 ምርጫ ጣቢያዎችና 2 ንዑስ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫውን ለማከናወን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ኮንታ ሌዩ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ዘገባ በምርጫው ከ60 ሺህ በላይ የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ የተመለከተ ሲሆን የተያያዙ እጆችና ጎጆ ለምርጫ ምልክትነት የቀረቡ መሆናቸው ታውቋል።

