ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ በተደረገው አሳፋሪ የእርስበርስ ጦርነት ተከትሎ ጦርነቱ ቀጥታ የተካሄደባቸው ትግራይና አማራና በከፊል አፋር ክልል የሚገኙ ዜጎች ልጆቻቸውን ከሞት በማጣትና አካል ከመገደል በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የዛ አከባቢ ህብረተሰብ ለከፍተኛ ራሃብና ድርቅ በመከሰቱና መንግስት ትኩረቱ አሁንም ጦርነት ላይ በማድረጉ ምግብ በማጣት እየሞቱ እንደሆነ የተለያዩ ሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት በአማራ ክልል “መብታችን እናስከብራለን” ከሚሉ ቡድኖች ጋር እየተደረገ ስላለው የእርስበርስ ጦርነት በተመለከተ “የድጋፍ ሆነ የተቋውሞ ዘገባዎችን ለምንድነው ከመስራት የተቆጠባችሁ” በሚል በተደጋጋሚ በርካታ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ወዳጆችና ተከታዮች በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እየጠየቁ ይገኛሉ።

እንደሚታወቀው በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ሶስት አመታት ከትግራይ ጋር ባደረገችው አስነዋሪ የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ሚሊዮኖች ሞተዋል፣ ሚሊዮኖች የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል እንዲሁም ሀገሪቱን ዕድገት ለበርካታ አመታት ወደኋላ የመለሰ የሀብት ውድመት አስከትሏል።

ከዚሁ አስከፊ የእርስበርስ ጦርነት በኃላ በተለይም ከደቡብ ዎላይታ አከባቢ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በጥቂት ፓለቲካኞች ሀሳብ ልዩነት ምክንያት በማያገባቸው መስዋዕት ሆነዋል፣ አጥንታቸው ተከስክሰው ደማቸው ፈሰው ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ለወላጆቻቸው በህይወት መኖራቸው ሆነ አለመኖራቸው ተረጋግጠው እርም እንዳያወጡ እንኳን አልተነገራቸውም እንዲሁም ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ድርድር ምዕራፍ ሲመጡ ጉዳት የደረሰባቸው ካሳ እንዲያገኙ መልሶ እንዲቋቋሙ በሚደረግበት ወቅት እንኳን ከፊት ሆነው መስዋዕትነት የከፈሉና አሳልፈው የሰጡ ቤተሰቦቻቸው ታሳቢ ሳያደርጉ በተገለሉት ወቅት ተጨማሪ ወጣቶች ለጦርነት እየተመለመሉ እንደ ዕድል ያተረፉም በግድ ወደ ጦርነት ሜዳ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል።

በተመሳሳይ ሁኔታ መንግሥት በአማራ ክልል ከሚገኙ “መብታችን እናስከብራለን” የሚሉ ቡድኖችም ትናንት በጦርነቱ ያለፉበትን ጉዳት ሳያስተውሉ፤ መንግስትም እንደመንግስትነት በሆደሰፊነት ልዩነትን ወደ መድረክ አምጥቶ ከመወያየት ይልቅ ጦርነትን በመምረጥ ከትናንቱ አሳፋሪና አስከፊ ጦርነት ጉዳት ሳንወጣ ሌላ የእርስበርስ ጦርነት እያካሄደ በመሆኑ WT ሚዲያ በዚሁ ሀገራችንን ወደኃላ የሚመልስ ታሪካዊ ስህተት እየተፈጸመ ባለበት ወቅት ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ከማበረታታት በቀር የትኛውንም ወገን ላለመደገፍ በሚል የድጋፍ ሆነ የተቋውሞ ዘገባዎችን ላለመስራት ውሳኔ ላይ በመድረሳችን መሆኑን እንገልፃለን።

ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ከአለም ሁሉ ወደኋላ የቀረችው በየጊዜው በሚከሰት እርስበርስ ጦርነትና ለጦርነቱ መሳሪያ ግዢ የሚታወጠው ከፍተኛ ገንዘብ ሲሆን ጦርነቱም በተለይም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ በፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት በተደጋጋሚ የሚከሰት በመሆኑ አብዘኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና ኦሮሚያ አከባቢዎች የማያውቁትና የማያገባቸው ጉዱይ ሲከሰት ልጆቻቸውን መስዋዕት በማድረግ እንዲሁም የሀገር ሀብት በጦርነቱ እንዲጎዳ በመደረጉ ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰ መሆኑን የተለያዩ ምሁራን ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በመከላከያ ሰራዊት አባልነት “ሀገሬን ከባዕድ ሀገር ለመጠበቅና ዜጎቼን ከጠላት ለመከላከል” በሚል የሰለጠኑ ፓለቲካኞች በሀሳብ ልዩነት በመለያየታቸው ብቻ እርስበርስ ጦርነት እንዲካሄድ በተፈጠረው ላይ እነኚያ ለሀገር ፍቅር ከፊት ተሰልፈው ህይወታቸውን ያጡ ከጥቂቶች በስተቀር እስከዛሬ በርካታ እናቶች “ልጄ ይመጣልኛል፣ ወይንም የት ወድቆ ይሁን” በሚል ጭንቅ ውስጥ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ የእነሱን የመርዶ ዜና (የደም ገንዘብ) የውሸት ሰነድ በማዘጋጀት የገቢ ምንጭ እያደረጉ መሆኑ ደግሞ ህዝቡም ለጦርነቱ እምቢ ለማለት የሚገባው ነጥብ ነው።

በመሆኑም በሀሳብ ልዩነት ምክንያት መንግስትና አማራ ክልል የሚገኙ እንዲሁም አንዳንድ ኦሮሚያ አከባቢ ወገኖች የጀመሩትን አሳፋሪ እርስበርስ መጠፋፋት ጦርነት በአስቸኳይ አቁሞ ችግሮች በውይይት ብቻ እንዲፈቱና ለውይይቱም ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያመቻች በተለይም መንግስት እንደመንግስትነት ነገሮቹን በሆደሰፊነት በማየት ከፍተኛ ድርሻ በመውሰድ የንፁሃን ሞትና የሀገር ሀብት ውድመት እንዲቆም እንዲያደርግ አጥብቀን ጥሪ እናደርጋለን።

በዛሬው እለት የአውሮፓውያን አዲሱ 2024 ዓመት በተለያዩ ዓለማት ሆነው እያከበሩ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆች እንኳን በሰላምና በጤና አደረሳችሁ እያልን በዓሉ የሰላም፣ የበረከት፣ እርስበርስ የመተባበር፣ የመቻቻል እንዲሁም ያቀድነው በሙሉ የሚሳካበት መልካም ዓመት እንዲሆን እየተመኘን ሀገር ወዳድ የሆነ ዜጋ በሙሉ በየትኛውም ሁኔታ ለጦርነት እምቢ በማለት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ኢትዮጵያን ከድንቁርናና ሁዋላ ቀርነት ለማውጣት ሁላችንም በያለንበት የየድርሻችንን እንወጣ እንላለን!! በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *