በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ከሀገሪቱ ለማባረር የሚደረግ አደገኛ ቅስቀሳ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ በፊት አለምአቀፍ ሀገራት ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ ቀረበ።

በኢትዮጵያ መንግስት እና በሶማሌላንድ መካከል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚደረግ ቅስቀሳ “በጣም ያሳስበኛል” ብሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ) በሶማሊያ ሀገር የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አክቲቪስቶች ሰላማዊ የኢትዮጵያ ዜጎችን እንዲከላከሉ ተማጽኗል።

በፓርቲው የውጭ ግንኙነት ፅህፈት ቤት እሁድ እለት የወጣው መግለጫ “ስደተኞች እና ሲቪል ዜጎች በሁለቱም ግንባሮች ላሉ ሰዎች አክብሮት እንዲኖራቸው በመጠየቅ ከሁሉም ወገን እንዲረጋጋ እና እንዲረዳ” በመጠየቅ ከዚህ ቀደም በነዚህ ሀገራት መካከል የተከሰቱት ተመሳሳይ ክስተቶች በኢትዮጵያ በተለየም በኦሮሞ ስደተኞች እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ማድረሱን አስታውሷል።

መግለጫው የወጣው የኢትዮጵያን ዜጎች በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብሄር “ኦሮሞ” ነው በሚል በተለይም ኦሮሞ የሆኑ ስደተኞችን ከሶማሊያ ለማባረርና ጉዳት ለማድረስ በማህበራዊ ሚዲያ እየተበራከተ የመጣውን ጥሪ እና ቅስቀሳ ተከትሎ መሆኑ ታውቋል።

ፓርቲው ከኢትዮጵያ የሚሰደዱት “በሶማሊያ ምንም ዓይነት መጥፎ ዓላማ እንደሌላቸው መገንዘብ አስፈላጊ” መሆኑን በመግለፅ “የፖለቲካ ውጥረት በበዛበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት፥ በሶማሊያ የሚኖሩ የኦሮሞ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንድከላከሉ” በሚል ተማፅኖ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ሁሉም ጎረቤት ሀገራት ሊነሱ በሚችሉ ግጭቶች ምክንያት “በአካባቢው ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱ በፊት” ጣልቃ እንዲገቡ አሳስቧል።

ሶማሊያ ሶማሊላንድን እንደ አንድ የራሷ ክልል ትቆጥራለች፦ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ቁርጠኝነት አሳይታለች፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ስምምነቱ ምንም አይነት ህግጋትን እና አለም አቀፍ መመዘኛዎችን የማይጥስ መሆኑን በመግለጽ ሌሎች ሀገራትም በቀጣናው የኢኮኖሚ አጋርነት መስራታቸውን ጠቁማለች።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት መሀሙድ በትናትናው እለት “ዛሬ ማታ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የፈረሙትን ህገወጥ የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ የሚያደርግ ህግ ፈርሚያለሁ” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

ፕሬዝደንቱ “ይህ ህግ በአለምአቀፍ ህግ መሰረት አንድነታችንን፣ ሉኣዊነታችንን እና የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው” ብለዋል።

ሰምምነቱ ሉኣለዊነትን የሚጥስ ነው የምትለው ሶማሊያ፣ በጉዳዩ ላይ ምክክር ለማድረግ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርታለች።

ፕሬዝደንቱ በዚሁ ጉዳይ በተሰበሰበው ፖርላማ ፊት ቀርበው እንደናገሩት የተፈረመው ስምምነት “ህግን የሚጥስ እና ተፈጻሚ የማይሆን” ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ሌሎች ሀገራት ከሶማሊያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የፈረሙት ስምምነት የሚጎዳው ሀገርም ሆነ የሚጥሰው ህግ እንደሌለ ገልጿል።

መንግስት ኢትዮጵያ ለባህር ኃይል የሚሆን የጦር ሰፈር ስታገኝ፣ ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምታገኝ ተስማምቷል።

መንግስት ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና መስጠትን በተመለከተ ኢትዮጵያ አጢና አቋም ትወስዳለች ብሏል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀይ ባህር የህልውና ጉዳይ መሆኑን እና ይህንንም ለማግኘት መደራደር ያስፈልጋል ካሉ በኋላ የባህር በር ጉዳይ አጀንዳ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት የኢትዮጵያን ጥያቄ በበጎ እንዲያዩት፣ ያ ካልሆነ ግን ቆይቶ ሊፈናዳ የሚችል የጸጥታ ችግር እንደሚሆን ማሳሰባቸው ይታወሳል።

የአትዮጵያ ህዝብ በ2030፣ 150 ሚሊዮን እንደሚደርስ እና ይህ ህዝብ ወደብ አልባ መሆን አይችልም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እንዲረጋጉ፣ ውጥረቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ እርምጃዎች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል።

 ህብረቱ የአባል ሀገራትን የግዛት አንድነትን እና ሉአላዊነት ማክበር አስፈላጊ ነው” ብሏል። በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተዘጋጀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *