የህንፃው ግንባታ ሂደት በቀድሞ በዎላይታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ብልሹ አሰራር ምክንያት በመስተጓጐሉ የሚመለከታቸው አካላት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ የሶዶ ደም ባንክ አገልግሎት ሰራተኞች ጠይቋል።

የዎላይታ ሶዶ ደም ባንክ አገልግሎት “የግንባታ በጀት ግለሰቦች ተደራጅተው ለግል ጥቅም ከማዋል ባሻገር ተቋሙ በብልሹ አሠራር ምክንያት ትልቅ ችግር ውስጥ ስላለ እውነተኛ መረጃ ለህዝብ ግልጽ እንዲደረግ” በሚል ሰራተኞቹ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያን ጠይቋል።

እንደ የደም አገልግሎት የሰራተኞቹ ተወካይ መረጃ ከሆነ የኢትዮጵያ ደም አገልግሎት የዎላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ 2009 ዓ/ም ከተቋቋመ ጀምሮ ምቹ ባልሆነ ቦታ በኪራይ ቤት እየሰራ የቆየ በመሆኑ የራሱን ህንፃ እንዲያስገነባ በፈደራል ተወስኖ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና ከክልል ጤና ቢሮ በርካታ ሚሊዮን ብር ግንባታው እንዲከናወን በሃላፊነት እንዲያስጨርሱ የተወከሉ የዎላይታ ዞን ፋይናንስና ጤና መምሪያ ሃላፊ ( አቶ አሳምነው አይዛ የአሁኑ የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤህ ኃላፊ ) መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ግን የግንባታ ሂደት እንዲመሩ የተወከሉ ግለሰቦች ከተቋራጮች እንዲሁም ከሌሎች አመራሮች ጋር በመመሳጠር ብሩን ለግል ጥቅም አውለው ግንባታው ሳይጠናቀቅ ለ7 ዓመት ቆሞ በመቅረቱ ምክንያት የተቋሙ በጀት 50% ያህል ( 480,000 ብር) ለቤት ኪራይ ስለሚከፈል ሥራው በአብዛኛው የመስክ ሥራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሠራተኞች ውሎ አበል መክፈል ስለማይችል ሥራው በመስተጓጐሉ የብዙ እናቶች ነፍሰ በደም እጥረት ምክንያት እየጠፋ እንደሚገኝ የሰራተኞቹ ተወካይ ተጨባጭ በሰነድ የተደገፈ መረጃ በማድረስ ጭምር አብራርተዋል።

አክለውም ተወካዩ “የተቋሙ የቀድሞ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ አብርሃም የራሳቸውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ስለማይመች ያለአንዳች ምክንያት ተንሳፋፊ አድርገው፤ ቅጥር ስፈፀም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማስታወቂያ ወጥቶ በክልሉ ጤና ቢሮ አማካኝነት መሆን ሲገባ በወቅቱ የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አሳምነው አይዛ እና የቀድሞ የዎላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ፣ የአሁኑ የክልሉ ብልፅግና ረዳት ተጠሪ አቶ ዮሐንስ በየነ ቤተሰብ የሆነ ግለሰብ ከሙያው ውጪ የሆነ ( Environmental science ) ለቦታው የማይመጥን ሰው ከወረዳ ጎትተው አምጥቶ ተቋሙ ከታቀደለት ዓላማ ይልቅ የካድሬዎች ዓላማ ማስፈፀሚያ ሆኖ ቆይቷል” ስሉ የችግሩን ጥልቀት በምሬት አስረድተዋል።

እንደ መረጃ ምንጩ ገለፃ “አሁን ባለው ሁኔታ የአመራሮቹ የብልሹ አሰራር ቅሌት ይፋ ለማድረግ የተቋሙ ሰራተኞች በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ሰነድ በጀመሩት የትግል እንቅስቃሴ ያለሙያው ተልዕኮ ለማስፈፀም ተሹሞ የነበረውን ግለሰብ በማሸሽ በክልሉ የተሻለ ቦታ ሰጥተው ካስኮበለሉ በኋላ በደም ባንኩ ውስጥ መምራት መሥራት የሚችሉ እጅግ በሙያው የተካኑ ባለሙያዎች እያሉ ለጊዜው ውክልና ብቻ በመስጠት ገበናቸውን መጠበቅ የሚችል ካድሬ ኃላፊ በቋሚነት ለመሾም እንቅስቃሴ ላይ ናቸው” በሚል ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊና ህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ እና የዎላይታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኤካ በብልሹ አሰራር ምክንያት የቆመውን ህንፃ ግንባታ ያለበት ደረጃ ምልከታ አድርገው ሰራተኞቹን ባወያዩበት ወቅት ግንባታው መጠናቀቅ ካለበት እጅግ በጣም የዘገየ መሆኑ የተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰፊ ችግሮች እየገጠመው መሆኑን በማስረዳት ግንባታው በአስቸኳይ እንድጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግና ለተቋሙ ህንፃ ግንባታ ለግል ጥቅም አውሏል የተባሉ አመራሮችና ግለሰቦች ወደ ህግ እግዲቀርቡ” ለማድረግ ቁርጠኝነት ማሳየታቸውን የመረጃ ምንጮቹ ጨምረው ገልፀውልናል። በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናከረ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *