
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ “የህዝብ ውክልና አንሷል” በሚል በውሸት በህዝብ ስም የግል ፍላጎት ካሳኩ በኃላ ለሌላ አሳልፈው መስጠቱ አነጋጋሪ ሆነ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳዳርነት የቢሮ መቀመጫውን አርባምንጭ ከተማ በማድረግ የተሾሙት አቶ ተስፋዬ ይገዙ “ተጨማሪ ስልጣን ይሰጠኝ” በሚል ከፍተኛ ውዝግብ በኃላ ቢሰጣቸውም ከስራው ጋር ምንም ግንኙነት ለሌለው ሰው ከአሰራር ውጪ ውክልና መስጠታቸው ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ልማትና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ሰራተኞች ገልጿል።
ነገሩ እንዲህ ነው አቶ ተስፋዬ ይገዙ “በክልሉ አስፈፃሚ አካል ውስጥ የዎላይታ ውክልና ተገፋ እኔም ዎላይታ ስለሆንኩ ተገፍቼ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ብቻ ተሰጥቶኝ አርባምንጭ የተወረወርኩት” በሚል በፌደራል ደረጃ ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸው አመራሮች ቢሮ በተደጋጋሚ በመመላለስ የዎላይታ ተወላጅ ከሆነው አቶ በረጋ ብራሃኑ የኢንተርፕራይዞች ልማትና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊነት ቦታ በመንጠቅ ተጨማሪ ስልጣን ማግኘቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያደረሱት መረጃ ያረጋግጣል።
አቶ ተስፋዬ “የህዝብ ውክልና አንሷል” በሚል በውሸት በህዝብ ስም የግል ፍላጎት ለማሳካት ባደረጉት ጥረት መልሰው የዎላይታ ተወላጅ የሆነውን ከስልጣን አስነስተው ቦታውን ነጥቀው ከምክትል ርዕሰ መስተዳዳርነት ጋር ደርበው ለመስራት ተጨማሪ ሹመት ቢሰጣቸውም በተቃራኒው የኢንተርፕራይዞች ልማትና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊነት ከአሰራር ውጪ በውክልና ለሌላ ብሄር መስጠቱ ተገቢ ያልሆነና የግለሰቡን በህዝብ ስም መነገድን እንዲሁም የተመደበበትን ቢሮ በጀት ለሙስና እንዲያመች ለማድረግ ስለመሆኑ የሚያመለክት እንደሆነ አንድ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ትዝብቱን አካፍለዋል።
የመረጃ ምንጫችን ምክንያቱን ሲያስረዳ፦ እውነትም “የህዝብ ውክልና በአመራር ፑል ውስጥ አንሷል” በሚል ታግለው ተጨማሪ ያገኘ ሰው ውክልና አንሷል በተባለው ብሄር ተወላጅ የተያዘውን ኃላፊነት ቦታ በመንጠቅ ሳይሆን “ከሌላው ይሰጠኝ ይላል” ፤ በተጨማርም በህጉ መሠረት ውክልናውን በኢንተርፕራይዞች ልማትና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ በመሆን እየሰሩ ለሚገኙት ለሆኑት አቶ ብርሃኑ ምንኤ (የዎላይታ ተወላጅ) ይሰጣል እንጂ አሁን ከተጠቀሰው ቢሮ ጋር በምንም የማይገናኝ ኃላፊነት ለያዙ የምክትል ር/መስተዳድሩ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ መስጠት “አግባብነት የሌለውና የግለሰቡ ገደብ የለሽ ስልጣን ጥማት መሻት የሚያመለክት” ስለመሆኑም አስረድተዋል።


በዚህም በግልጽ ቋንቋ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በህዝብ ስም ለመነገድ “ውክልና አንሷል” በሚል የሄደበት ርቀት ውሸት መሆኑ የሚረጋገጠው የዚህ ሽኩቻ ሰለባ የተደረጉት የኢንተርፕራይዞች ልማትና ሥራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት የዎላይታ ተወላጅ አቶ ቢረጋ ብርሐኑ “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሉዋት” እንደሚባለው ከሥር በፎቶው እንደምታዩት ቡሉኮ ተሸልመው የተሰናበቱ ሲሆን በውጤቱም ዎላይታ አንድ የአስፈፃሚነት ወንበሩን አጥቷል።
ይሄን ዜና ያቀረብንበት ዋናው አላማ በክልሉ “የዎላይታ ተወላጆች በቂ ውክልና አላቸው” የሚለውን ለማሳየት ወይንም የዎላይታ አመራርነት ቦታ “ለሌላ ብሄር ተሰጥቷል” የሚለውን ለማንፀባረቅ ሳይሆን የአቶ ተስፋዬ ይገዙ በህዝብ ስም ለመነገድ የሄዱበት ርቀትና ትግላቸውም፦ በአከባቢው የመንግስትን መዋቅር ተክተው በእሳቸው መርነት የተደራጀ የአመራር ምደባ ስርዓት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ይከተላል ከሚባለው ዕሳቤና አሰራር ውጭ በአቤ-ልጅ ኔትወርክ፣ በአከባባዊነት ኔትወርክ፣ በትውውቅ እና በጥቅም ላይ በተመሰረተ እንዲሁም በቤተሰባዊ ኔትዎርክ እየተመራ የቀረበ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ እንደሆነ እናሳውቃለን።
በተቃራኒው በዎላይታ ቀጥታ ከመንግሥት ዩንቨርስቲ በዲግሪ የተመረቁ ወደ 150 ሺህ የሚጠጉ እንዲሁም ከ70 ሺህ በላይ ከግል ኮሌጆችና ከመንግሥት በዲፕሎማ የተመረቁ ስራ አጥ ወጣቶች፣ 10ኛ እና በ12 ኛ ክፍል አጠናቀው ወደ ዩንቨርስቲና ኮሌጅ ሳይገቡ የቀሩ፣ እንዲሁም ዘርፈብዙ ምክያቶች በፈጠሩት ዳፋ ሴቶችና ህፃናት በሚያሳዝን ሁኔታ በሀገሪቱ በሁሉም ጎዳናዎች ላይ ተበታትነው ቢገኙም በአከባቢው ከውትድርና ውጪ ያለው የቅጥር ሆነ ሌላ የስራ ዕድል ቢሆንም በገንዘብ፣ በአመራሮች ዝምድና፣ በአከባቢዊነት እንዲሁም በትውውቅ በመሆኑ እንዲሁም ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል እንድም ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ሌላ ፋብሪካዎች አለመኖር ብቻ ሳይሆን በፌደራል፣ በክልል ሆነ በዞኑ አመራሮች ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ተብሎ የተቀረጸ ዕቅድ ሆነ አላማም አለመኖሩ ወጣቶቹ በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ ስለመሆኑም በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው