የአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣት አፍሪካውያን አመራሮች ውስጥ ተካተተች።

ከኢትዮጵያ አልፎ በአለምአቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን ላይ የምትገኘው ወጣት ቢታኒያ ሉሉ ብርሃኑ ከ2023 ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣት አፍሪካውያን አመራሮች ውስጥ ከመካተቷ በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር የወጣቶች የመጀመሪያ አፍሪካዊ ልዩ አማካሪም ለመሆን የበቃች ናት።

ቢታኒያ በወጣቶች ቅድሚያ የተሰጣቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት በአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤት በተቋቋመው ላይ የፕሮግራም ዳይሬክተር ስትሆን በአፍሪካ በወጣቶች ከሚመሩ ተቋማት መካከል በአመራርነት ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የምትገኝ ውጤታማ ወጣት ሆና ተመርጣለች።

ቢታንያ ሉሉ በወጣት ልማት ዘርፎች እና በፖሊሲ ጥብቅና፣ በጤና፣ በፆታ እና በትምህርት ውስጥ በማካተት የበለጸገ ልምድ ያላት ዓለም አቀፍ ወጣት መሪ ስትሆን በአህጉራዊና አለምአቀፋዊ ፖሊሲዎች እና ፕሮጄክቶች ውስጥ ቁልፍ ሚናዎችን በመጫወት ከሃገራት መሪዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች ጋር ውይይቶችን በመምራት እና ወጣቶች እና ሴቶች በህዝባዊ ፖሊሲ ውስጥ እንዲሳተፉ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ በርካታ አጋርነቶችን ስትፈጥር እንደቆየች ከግል ማህደሯ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያረጋግጣል።

ወጣቷ ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት እና በማስተባበር በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በዓለም ዙሪያ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሥራቷ ለዘላቂ ልማት ባላት ቁርጠኝነት በታዋቂ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች እውቅና ያገኘች በተጨማሪም እንደ እ.ኤ.አ. በ 2021 በ100 በጣም ተደማጭነት ባላቸው ወጣት አፍሪካውያን ዝርዝር ውስጥ መካተት ችላ እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ቢታኒያ ከአውሮፓ ጄኔቫ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ በዓለም አቀፍ/ግሎባል ጥናቶች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ በሰው እና የኢኮኖሚ ልማት በአፍሪካ፣ ከአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪ በኤሌክትሪካል እና ኮምፒውተር ምህንድስና እንዲሁም ከተለያዩ አለምአቀፋፍ ዩንቨርስቲዎች ዲፕሎማ በማግኘት የተመረቀች ናት።

ይህቺ በወጣትነቷ በአመራርነት የአለምአቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን የምትገኘው በአፍሪካ ወጣቶች ተሟጋቾች እና የወጣት ድርጅቶች በሀገር ውስጥ እና በአፍሪካ ቀንድ የፖሊሲ አሰራሮች እንዲቀይሩ፣ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች እንዲፈቱ እና አቅማቸውን እንዲያሳኩ የአቅም ማጠናከሪያ ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የአማካሪነት፣ የአሰልጣኝነት እና የትብብር ግንባታ ድጋፍ በማድረግ ባደረገችው ተግባር አመርቂ ውጤት በማስመስገቧ በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2023 በአፍሪካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ 100 ወጣት አመራሮች መካከል አንዷ በመሆን ተመርጣለች።

ወጣት ቢታኒያ በአለምአቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን አጠናክራ የቀጠለች ስትሆን በሌሎች በጎ ተግባር ላይ የተሰማራች እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *