እርሰዎ ምን ይላሉ ? ክቡርነትዎ ዛሬ ትንሽ እስኪ እንጠይቀዎት🙏 ለመሆኑ እርሶዎ የአንድ ሊቃ ትምህርት ቤት አጥር ግንባታ የመላው ዎላይታ ትምህርት ዘርፍ ስብራት ይጠግናል ብለው ይገምታሉ ? እርስዎ ከክንዶ ዲዳዬ እስከ ድምቱ፥ ከሀማሳ እስከ አቹራ ድረስ 99.99 ከመቶ በላይ ተማሪዎች ጉዳይ ትኩረት ተነፍጎ ለአንዱ ብቻ ከመንግሥት አመራር እስከ ዕድር መሪ መደበኛ ስራ ቁጭ አድርጎ ለአንድ ብቻ እየጮሁ ሲውሉ ጤናማ አካሄድ ይላሉ❓

ለመሆኑ እርስዎን በዎላይታ ቀጥታ ከመንግሥት ዩንቨርስቲ በዲግሪ የተመረቁ ወደ 150 ሺህ የሚጠጉ እንዲሁም ከ70 ሺህ በላይ ከግል ኮሌጆችና ከመንግሥት በዲፕሎማ የተመረቁ ስራ አጥ ወጣቶች፣ 10ኛ እና በ12 ኛ ክፍል አጠናቀው ወደ ዩንቨርስቲና ኮሌጅ ሳይገቡ የቀሩት ጉዳይ በጓዳ ተደብቀው ባለበት የሊቃ አጥር ግንባታ አጀንዳ መሆኑ አያስገርሞዎትም❓

ቆይ እርስዎን ሴቶችና ህፃናት በሚያሳዝን ሁኔታ በሀገሪቱ በሁሉም ጎዳናዎች ላይ ተበታትነው ቢገኙም በአከባቢው ከውትድርና ውጪ ያለው የቅጥር ሆነ ሌላ የስራ ዕድል ቢሆንም በገንዘብ፣ በአመራሮች ዝምድና፣ በአከባቢዊነት እንዲሁም በትውውቅ ሆኖ ሳለ በተቃራኒው ያ ተዳፍኖና ዝም ተብሎ የአንድ ትምህርት ቤት አጥር ግንባታ አጀንዳ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሲያዩ ምንም አይሰማዎትም❓

የማከብርዎት እርስዎን እየጠየቅን ነውኮ፦ ቆይ በዎላይታ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችል እንድም ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ሌላ ፋብሪካዎች አለመኖር ብቻ ሳይሆን በፌደራል፣ በክልል ሆነ በዞኑ አመራሮች ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ተብሎ የተቀረጸ ዕቅድ ሆነ አላማም አለመኖሩ ወጣቶቹ በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ እያዳረገ መሆኑ ምንም አያስጨንቆዎትም ❓

ክቡርነትዎ የዎላይታ ታይምስ እንደ አንድ የአከባቢውን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ እንደሚሰራ ሚዲያ እየጠየቀ የሚገኘው፦ በአከባቢው አብዛኛው አሰራር የመንግስትን መዋቅር ተክተው በአቤ-ልጅ ኔትወርክ፣ በአከባባዊነት ኔትወርክ፣ በትውውቅ እና በጥቅም ላይ በተመሰረተ እንዲሁም በቤተሰባዊ ኔትዎርክ እየተመራ የህዝብ አንድነት አደጋ ላይ እየወደቀ ስለመሆኑ ለእርስዎ መቼ ነው ጉዳዮዎት የሚሆነው ❓

99.99% የሚሆነዉ የዎላይታ ሕዝብ ልጆች የሚማሩት የመንግስት ት/ቤቶች አካላዊ ገጾታ ከታች ያለውን ይመስላል። ወይንም ከዚህ የከፋም ነዉ። ይሁን እንጂ ከላይ በዝርዝር የተነሳው አይነት የህዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮች ተዳፍነው ሴራኞቹ ለማምለጥ በሊቃ አጥር ግንባታ አጀንዳ ውስጥ ተደብቀው የመንግስት መደበኛ ኃላፊነት ወደጎን በመተው ሊቃ፣ ሊቃ፣ ሊቃ ማለታቸው ለእርስዎ እውነትም ለሊቃ ውግንና የሚሆኑ ይመስሎታል❓

ቆይ እርሰዎን በዎላይታ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ባለፉት አራት አመታት “በቅርቡ ይሰራሉ” ተብሎ ለድዛይን ብቻ በርካታ ገንዘብ ወጥተው ይፋ የተደረጉ የአባላ አባያ Summer city፣ የዩንቨርስቲው ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የአረካ የግብርና ልህቀት ማዕከል፣ የቦዲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል በዝምታ መቆሙ ምንም አያሳስበዎትም ❓

ግድ የለዎትም እንጠይቀዎት እስኪ ጨምረንም፦ ቆይ ክቡርነትዎ ለእርሰዎ ከንግግር ያላለፉ ለድዛይን ብቻ በርካታ ገንዘብ የወጣበት የዎላይታ የቀድሞ ነገስታት መታሰቢያ ሀውልት፣ የወይቦ መስኖ ፕሮጀክት ግንባታ፣ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በሶዶ ከተማ ይገነባል የተባለው የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ግንባታ፣ ዘመናዊ የመርካቶ ገበያ ማዕከል ግንባታ፣ መለስተኛ እንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ፣ ለምርጫ ቅስቀሳ ዜና የተሰራው ከግብርና ኮሌጅ እስከ ሌዊ/ኮካቴ የሚገነባው የመንገድ ግንባታ በተጨማሪም በየከተማ አስተዳደርና ወረዳዎች ለህብረተሰቡ “በቅርቡ ተጀምሮ ለአገልግሎት እንዲበቁ እናደርጋለን” ተብሎ ይፋ ቢደረግም ከቃል ያላለፉ ፕሮጀክቶች ጉዳይ እንዴት ለእርስዎ አጀንዳ ሊሆን አልቻለም❓

በ2012 ዓ.ም መላውን የዎላይታ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የሰሙትንም ሁሉ ቀልብ የሳበ የዞኑ መንግስት በዎልማ በኩል ለማከናወን የተለያዩ ቅድመ እቅዶች ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ለመግባት ግልጽ አላማ፣ ዕቅድና ግብ በማውጣት በይፋ “የዎላይታ እንዱስትሪ አብዮት” በሚል ተጀምሮ በሚገርም ሁኔታ በአንድ ቀን ብቻ በመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ዎላይታ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የመንግስት መዋቅሮች በተሳተፉበት ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ የተቻለበትና በራስ አቅም ችግሮቹን ለመፍታት በአንድነት የተጀመረውን ንቅናቄ ለመደገፍ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የአከባቢው ተወላጆች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ አርሶአደሮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ድጋፍ ለማድረግ በቁጭት በተነሱበት ወቅት ዕቅዱ በመሀል ተግባራዊ እንዳይሆን በወቅቱ በአከባቢው በተፈጠረው ፓለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የቆመው ለምን ብለው ለምን አይጠየቁም ❓

ክቡርነትዎ፥ የዎላይታ ህዝብ በአንድነት በአከባቢው በህዝብ ተሳትፎ ብቻ ከዚህ በፊህ የሰራቸውን ልማት ስራዎች ህያው ምስክሮችን እያወቁ ፦ ግልጽ አላማና ግብ ተቀምጦ በይፋ ከጀመረ በኃላ በአንድነት የሚያሰልፍ አጥተው ዝምታ የመረጡ ልጆቿ በቁጭት እንደየአቅማቸው በመደገፍ ታሪካዊ ገድል እንዲፈፅሙ ለምን በ2012 ዓ.ም መላውን የዎላይታ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የሰሙትንም ሁሉ ቀልብ የሳበና የተለያዩ ቅድመ እቅዶች ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ለመግባት ግልጽ አላማ፣ ዕቅድና ግብ በማውጣት በይፋ ተጀምሮ በዎላይታ ልማት ማህበር ቢሮ መደርደሪያ ላይ ቁጭ ያለውን “የዎላይታ እንዱስትሪ አብዮት” ሰነድ በድጋሚ ተከልሶ ለህዝብ ይፋ ተደርጎ የድጋፍ ንቅናቄ በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ እርስዎ ለምን ትኩረት አያደርጉም❓

በናትናኤል ጌቾ ቤታሎ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *