በዎላይታ ዞን የኤችአይቪ በሽታ ለመቆጣጠር ከመንግሥት ሰራተኞች የተሰበሰበ ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለአመራሮች ለውሎ አበል መዋሉ ተነገረ።

የኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ለተገኘባቸው ሕሙማንን ለመደጎም እና ለሕብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለመሥራት ይቻል ከመንግስት ሠራተኞች በፔይሮል ተቆርጦ የሚከፈለው የ0.5% የኤች አይቪ/ኤድስ ፈንድ በዎላይታ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተሞች 30 ሚሊዮን 860,995 ብር ከታለመለት ዓላማ ውጭ አመራሩ ለውሎ አበል እና ለሌሎች ሥራ ማስኬጃ እንደዋለ የዎላይታ ዞን ጤና መምሪያ ሪፖርት ማመልከቱን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከሰነዱ አረጋግጧል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከባለበጀት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የኤች አይቪ ሜይንስትሪሚንግ በጀት (2%) ገና በጀት ስደለደል በሐምሌ ወር ተቆርጦ በየመዋቅሩ ፋይናንስ ሴክተር አካውንት ገቢ የሆነው 42 ሚሊዮን 625,000 ብር በድምሩ ከየኤችአይቪ ኤድስ ፈንድ (0.5%) ከተመዘበረው ጋር ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለውሎ አበል መዋሉንና አላአግባብ መባከኑን በሪፖርቱ ተገልጿል።

በህገወጥ መንገድ የኤችአይቪ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ተቆርጠው የተሰበሰበውን 73 ሚሊዮን በላይ የገንዘቡን መጠን የሚገልጸውን ቦታ መረጃው እንዳይወጣ በማለት ቢያስቀሩም የዞን፣ የ16 ወረዳዎች እና የ7 ሪፎርም ከተሞች በዝርዝር ለውይይት ቀርቦ ከነበረው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሰነዱን ማግኘት ችሏል።

በዞኑ በሽታውን ለመከላከል እና በበሽታው ለተጠቁት ድጋፍ ለማድረግ ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ በዎላይታ ዞን 5,218 ያህል ሰዎች ኤች አይቪ በደማቸዉ እንደሚገኝ እና 4,675 (90%) (DHIS-2, ታህሳስ 2016) ሰዎች የፀረ-ኤች አይቪ ሕክምና አገልግሎት እየተከታተሉ እንደሚገኙ የዎላይታ ዞን ጤና መምሪያ በቀን 09/8/2016 ዓ.ም በዎላይታ ሶዶ ከተማ ባደረገው የውይይት መድረክ ያቀረበው ሪፖርት ያመላክታል፡፡

በዞኑ ባለፉት 6 ወራት በተካሄደ የኤች አይቪ ምርመራ 176 አዳዲስ ሰዎች ኤች አይቪ በደማቸዉ እንደተገኘባቸው መረጃዎች የሚያመለክት ሲሆን የኤችአይቪ ምርመራ ልየታ መጠን ከስታንዳርዱ በታች እና እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው እንጂ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ከፍ ልል እንደሚችልም ሪፓርቱ አመላክቷል።

ወላጆቻቸውን በኤችአይቭ ካጡ ወላጅ አልባ ሕጻናት እና በበሽታው ታሞ አቅም ካጡ ምስኪኖች ጎሮሮ በመንጠቅ “ሀፍረተቢስ የሆነው የአከባቢው አመራሮች የዎላይታን ሕዝብ ደምን እንደ ትዋን መጥጦ ከጨረሰ በኃላ አጥንቱን እየቆረጠመ” እንደሚገኝ ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ በሽታ ያጡ ወላጅአልባ ሕጻናት ደጋፊ በማጣታቸው ለልመና ወደ ጎዳና የወጡት ወገኖች ህይወት ህያው ምስክር እንደሆነ በርካቶች ይስማሙበታል።

የበሽታውን ስርጭት፣ ሕመም እና ሞትን ከማስቀረት አኳያ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት እጅግ ደካማ እና ከፍተኛ ውስንነቶች የተመዘገቡበት ሲሆን የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ እየተሠሩ ያለ ሥራዎች ዝቅተኛ በመሆኑ የበሽታውን አጋላጭነት የሚጨምሩ ሁኔታዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ችግሩን ውስብስብ በማድረግ አፍላና ታዳጊ ወጣቶች ላይ ማህበራዊ ሚዲያ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ ብቻ ማየቱም ተገቢ ይሆናል፡፡

በመሆኑ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አላአግባብ የባከኑ የኤች አይቪ ኤድስ ፈንድ እና ከባለበጀት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተቆርጦ በፋይናንስ አካውንት ገቢ የተደረጉ የኤች አይቪ ሜይንስትሪሚንግ በጀት ገንዘብ በገለልተኛ አካል ኦዲት ተደርጎ ገንዘቡ ተመላሽ በመደረግ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እና አጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እያሳሰብን ለውድ ተከታዮቻችን ደግሞ ጉዳዩ የደረሰበትን ተከታትለን እንደምናቀርብ ከወዲሁ እናሳውቃለን።

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *