ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሌለበት አስገድደው የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውን እንዲከተሉ ማድረግ የግለሰቦችን ድምፅ ለማፈን ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የተግባቦትና ጋዜጠኝነት መምህር ገልጿል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ “ማህበራዊ ሚዲያ ተከታይ በማሳደግ ዘመቻ” ላይ ከ450 ሺህ በላይ ተከታይ ለማፍራት ያለመ ንቅናቄ በፓርቲው አመራሮች ደረጃ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ይሄንን በክልሉ ለተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተሰጠውን ተልዕኮ በብርሀን ፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኙት መካከል “የግለሰቦችን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በማፍን” የሚታወቀው ዎላይታ ዞን ሰሞኑን እስከ ቀበሌ ድረስ በግንባር ቀደምትነት “ከ200 መቶ ሺህ በላይ ተከታይ ለማፍራት” በሚል መደበኛ የመንግስት ስራ ወደጎን በመተው ዘመቻ ላይ ይገኛሉ።

ዘመቻውን በበጎ የሚወስዱ እንዳሉ ሁሉ ለሚዲያ ዘርፍ በቅርበት ያሉ ግለሰቦች በተለይም አንድ በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የተግባቦትና ጋዜጠኝነት መምህር በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው “የሚዲያ ስራ በርካታ ተከታይ በማፍራት ብቻ ሳይሆን በሙያ የተደገፈ እውነተኛ፣ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊ እንዲሁም ተጨባጭ መረጃዎችን በግልፀኝነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ እየተሰራ በሂደት ተቀባይነት እያገኘ ሲሄድ ተከታዮቹ በፍላጎታቸው በሚከተሉት ጊዜ እያደገ የሚሄድ እንደሆነ ይገልፃሉ።

እንደ መምህሩ ገለፃ፦ በየትኛውም አለም ላይ እንዲዚህ “ብዙ ተከታይ የማፍራት ዘመቻ” ተብሎ ከዘርፉ ሙያ ጋር ምንም ግንኘነትና እውቀቱ የሌላቸው አመራሮችና ግለሰቦች መደበኛ ስራቸውን ትተው በዚሁ መንገድ መጠመዳቸው አሳፋሪ ተግባር ነው” በማለት ያስረዳሉ።

በተጨማሪም የዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በማይከበርበት ወይንም የፕሬስ ነፃነት በሌለበት አከባቢ በዘመቻ መልክ ዜጎችን አስገድደው የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውን እንዲከተሉ ማድረግ የግለሰቦችን የመብት ጥያቄ ድምፅ ለማፈን ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርም የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የተግባቦትና ጋዜጠኝነት መምህር በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተናግረዋል።

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *