በዎላይታ ዞን ከ70 ፐርሰንት በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግቷል፤ አብዛኛው የመንግስት ሰራተኞች ስራ አቁመዋል” የዎህዴግ ሊቀመንበር

ሊቀመንበሩ “የገጠሙን አንገብጋቢ ችግሮች
ሁሉ አካታች ዞናዊ ውይይት ካልተደረገ አደጋው እየተባባሰ በመምጣት የሁላችንም ደጃፍ ረግጦ መቆጣጠር ተስኖን አደጋ ላይ ከመውደቃችን በፊት ሁላችንም መንቃት አለብን” ብለዋል።

የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጎኣ በአከባቢው ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አጭር መግለጫ ሰጥተዋል።

ሊቀመንበሩ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ ላይ “በዎላይታ ውስጥ 70% የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በተማሪዎች መፃሀፍት እጥሰትና በመምህራን ደሞወዝ ባለመከፈሉ የመማር ማስተማር ሥራ ያቆሙ ሲሆን በሁሉም ወረዳዎች በመድኃኒት እጥረትና የሠራተኞች ደመወዝ መጥፋት ምክንያት ጤና ጣቢያዎች በከፊል ሥራ እያቆሙ ነው” በሚል አስረድተዋል።

በዞኑ መምሪያዎች ለአብነት ያህል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤትን ጨምሮ የመንግስት ሠራተኞችን በማስታወቂያ ከሰው ሀብት ውጭ ሌሎች ሠራተኞች ቢሮ እንዳይገቡና በቤታቸው እንዲሆኑ ትዕዛዝ እየተላለፈ እንደሆነም አቶ ጎበዜ ገልጸዋል።

የመንግስትን ሥልጣንና በጀት የሚመራ ተቋም ለተማሪዎች መመሪያ መጽሐፍ ማሳተም አቅቶት “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” የሚል የእርዳታ ዘመቻ ማድረግ በቀጣይ የሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ መጫወትና ዕጣፈንታቸውን ማምከን እንደሆነም ተናግረዋል።

ሊቀመንበሩ በሰጡት አጭር መግለጫ “የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለ እጅ መንሻና ጉርሻ አገልግሎት በማይሰጡበትና የከተማ መሬት በጥቂት ቡድኖች በሚዘረፍበት በዚህ ሰዓት ከዚህ ውድቀት እንዴት እንውጣ የሚል ሁሉ አካታች ዞናዊ ውይይት ካልተደረገ አደጋው እየባሰ በመምጣት የሁላችንም ደጃፍ ረግጦ መቆጣጠር ተስኖን አደጋ ላይ ከመውደቃችን በፊት ሁላችንም መንቃት አለብን” ብለዋል።

በተጨማሪም አቶ ጎበዜ “የዎላይታ ቀጣይ ትውልድ እጣፈንታና ብቸኛ አማራጭ የሆነው የትመረህርት ሰክተር መውደቅ እንደ ህዝብ የመቀጠል ተስፋችን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ሁላችንም ተረባረብን ሰክተሩን ማዳን ህልውናችንን ማዳን እንደሆነ ማወቅ ይጠበቅብናል” በሚል ጥሪ አቅርበዋል።

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *