ህዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይጥል በሚያደርግ አካሄድ የተዘረጋው የግለሰቦች መዋቅር እንዲፈርስ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዎላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ አባላት ገልጿል።

የዎላይታ ህዝብ በሌብነትና በጥቅም ትስስር መንግስታዊ መዋቅርን ተክቶ የተደራጀው የዚሁ የኔትወርክ ቡድን በፈጠረው ዳፋ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ዕጦትና በደል እየደረሰበት ስለመሆኑም በወቅታዊ ጉዳይ አስተያየት የሰጡ የገዢው ፓርቲ አባላት የተናገሩት።

የተጀመረው እርምጃ የመውሰድ እንቅስቃሴ፦ “የአመራሩ ምደባ ከብልጽግና ዕሳቤ እና አሰራር መሪህ ውጭ በአበ-ልጅነት ኔትወርክ፣ በአከባባዊነት ኔትወርክ፣ በትውውቅ እና በጥቅም ላይ የተመሰረተ የቤተሰባዊ ኔትወርክ በመሆኑ በየአካባቢው በተደራጀ ሁኔታ በከተማ እና በገጠር መሬት ዘረፋ፣ የተጀመሩና ለመጀመር የታቀዱ የተለያዩ ልማቶች የሚበጀተውን ገንዘብ ለአመታት እያጓተቱ ያለጠያቂ ተከፋፍለው መብላት እየተለመደ በሆነበት መሆኑ የረፈደ ቢሆንም የሚበረታታ ነው” በሚል አባላቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልጸዋል።

“በአከባቢው የጎጥና የግል ጥቅም ሰንሰለት መሠረት የተዘረጋው ቡድን የዎላይታን ሕዝብ በብረት በትር ቀጥቅጦ መግዛት ከጀመረ እነሆ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ከመንግሥት ሆነ ከፓርቲ፤ ከምንም ከማንም የበላይ ነን ብለዉ የሚያስቡና የሚንቀሳቀሱ ናቸዉ። ከምንም እና ከማንም እንበልጣለን ብለዉ ስለሚያስቡ የህዝብ አንድነት አደጋ ላይ በሚጥል መንገድ ማንኛዉም የዎላይታ ተወላጅ እሺ፣ አሜን ብሎ እንዲገዛላቸዉ ይፈልጋሉ” ሲሉም ስለ ቡድኑን ባህሪ አክለዋል።

“በተጨማሪም የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ በወቅቱ አያገኝም። በደህና ጊዜ ከመንግስት ሰራተኛዉ ወርሃዊ ደመወዝ ላይ የተቆረጠዉን የጡረታ፣ የኤች አይ ቪ፣ የስፖርት ወዘተረፈ ገንዘብ እንኳን ተቀራምተዋል። ለማህበረሰብ ጤና መድህን የተሰበሰበዉ ገንዘብም ለግላቸው አድርገዋል። የከተማ መሬት ዘርፈዋል፤ ወይም ሸጠዉ ተከፋፍለዋል። ድንጋይና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን ቀጥቅጠዉ በጆንያ ሞልተዉ የአፈር ማዳበሪያ ነዉ ብለዉ ለአርሶአደሩ ሸጠዋል። ለገጠርና ከተማ ልማት ፕሮጄክቶች የተመደበዉን በጀት ተቀራምተዋል” በማለት የችግሩን ጥልቀት በሰፊው አትተዋል።

በዚሁ ህዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይጥል ሲያደርጉ በነበሩ ቡድኖች ምክንያት የዎላይታ ዞን ከየትኛውም አከባቢ በላይ ሚዲያዎች፣ ህዝብ ውግንና ያላቸው አመራሮች፣ የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም ወጣቶች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት ተጠቅመው የሚስተዋሉ መንግስታዊ አሰራርና ብልሽት ላይ በሰላማዊ መንገድ ትችት በሚያደርጉበት ወቅት በህገወጥ መንገድ በማፈን፣ በማሰር፣ ያለጥፋታቸው ፍርድቤት እንዲመላለሱ በማድረግ እንዲሁም በስደት ከአከባቢው እንዲሸሹ የሚያስገድድ መሆኑንም አንስተዋል።

“በዞኑ ከተመረቁ 5 ዓመት እና በላይ የሆናቸዉን ከመቶ ሺህ በላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ድግሪ ምሩቃን እና አሁንም ሥራ አጥ ሆነዉ በአከባቢው ምንም አይነት የስራ ዕድል የለም፦ ይህ ችግር ደግሞ የሚመነጨው የአከባቢውን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት አመራርነት የተመደቡ ግለሰቦች የራሳቸውን ጎሳና ዘመድ ብቻ ለመጥቀም እየሰሩ መሆኑ በፓርቲው ላይ እምነት እንዳንጥል እያደረገ ነው” ሲሉም ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አባላት ቅሬታ ያቀረቡት።

በሌላ በኩል መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በማህበር ተደራጅተው መሬትን በምደባ የሚሰጥበት መልካም አሠራር እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በዎላይታ ሶዶ ከተማ አንዳንድ የዞን እና የከተማ አመራሮች በሞቱ ሰዎች ስም፣ በቤት ሠራተኞቻቸው ስም፣ በገጠር ወረዳ በሚገኙ አርሶአደር ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ስም፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች ስም፣ ሕገወጥ ማህበራትን በማደራጀት፣ የተጨብረበረ ሐሰተኛ የባንክ ስሊፕ በማቅረብ፣ የተደራጁበትን ቀን ወደኋላ በመጻፍ ውድና ውስን የሕዝብ ሀብት የሆነውን የከተማ መሬትን መመዝበራቸው እንዲሁም ከ10 ዓመት በላይ መሬቱን ሳያለሙ በእጃቸው ይዘው ያቆዩ፣ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ለሌሎች የሚያስተላልፉ፣ የሚሸጡ፣ ካርታና ፕላን አስይዘው ከባንክ ብድር የሚወስዱ እንዲሁም ሌሎች እንዳያለሙ ቦታውን በመያዝ የአከባቢ ዕድገት ማነቆ ሆነው መቆየቱንም ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በዎላይታ ዞን ከብልጽግና ፓርቲም ሆነ ከመንግስት በበለጠ የሚፈራውና የመንግስት ሆነ የፓርቲውን ቅቡልነት እንዲያጣ ባደረገው እንዲሁም በአከባቢው መንግስታዊ አደረጃጀትን ተክቶ በዘረጋው በዚሁ አደገኛ የግለሰቦች አደረጃጀት ለማረም የፈደራል እና የክልል መንግስት ጋር በመተባበር የጀመረው መልካም ጅምር የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *