በተጠረጠሩበት ህገወጥ ተግባር ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩና እንዲወገዱ ውሳኔ የተወሰነላቸው አመራሮች በአከባቢው ሁከት እንዲፈጠር እየቀሰቀሱ እንደሆነ ተገለፀ።

በዎላይታ ዞን የመንግስትን መዋቅር ተክተው በአበ-ልጅነት ኔትወርክ፣ በአከባባዊነት ኔትወርክ፣ በትውውቅ እና በጥቅም እንዲሁም በቤተሰባዊ ኔትዎርክ ካደረገው ህቡዕ አደረጃጀት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላቸው አመራሮች ላይ የፈደራል መንግስትና የክልሉ መንግስት በገለልተኛ ቡድን አጣርቶ በወሰነው ውሳኔ ያልተደሰቱት ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ህዝብን ለአመጽ እየቀሰቀሱ እንደሆነ የአደረጃጀቱ ዋና መሪ በሚያስተዳድረው ማህበራዊ ሚዲያ ከሚተላለፉ መረጃዎች ለመረዳት ሞክረናል።

በዚሁ ህገወጥ አደረጃጀት ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መነሻ የሆነው ሰሞኑን በአከባቢው በተጠርጣሪዎቹ አመራሮች ላይ ከከፌደራል በተመደበ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን የተደረገው ሪፓርት ለክልልና ለፈዴራል መንግስት መቅረቡን ተከትሎ እንደሆነ የተነገረ ቢሆንም “ዎላይታ ስለሆንኩ ተገፋው” በሚል እንዲሁም ብሄርን ከብሄር ጋር ለማጋጨት ህዝብን ለአመጽ እየቀሰቀሱና ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነም የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተመልክቷል።

ይሄንን መነሻ አድርገን አንድ የዎላይታ ሶዶ የህግ መምህር በጉዳዩ ላይ ተጠይቆ “ማነኛውም ሰው በህገወጥ ተግባር ከተሳተፈ በህግ ይጠየቃል፤ ለሌባ ብሄር የለውም፣ ሌቦች ሲያዙ በብሄር ጉያ ለመደበቅ የሚደበቁበት አካሄድ በአብዛኛው ቦታዎች የተለመደ ማምለጫ ዘዴ” እንደሆነ አስረድተዋል።

የህግ ባለሙያው አክለውም መንግስት “በእነዚህ ሌብነት ሰንሰለት ላይ እየወሰደ ያለው እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል በተቃራኒው ግለሰቦቹ ሌብነታቸውን ለመደበቅና ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሲሉ በአከባቢው ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጥሩ ዕድል መስጠት የለበትም፤ ሰላም ወዳዱ ህዝብም በሌቦች ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍና ደስታ እየገለፀ ይገኛል” ብለዋል።

በአጣሪ ቡድን በተደረገው ምርመራ በህገወጥ አደረጃጀትና ተግባር ላይ መሰማራታቸው ለክልልና ለፌደራል መንግስትም ቀርቦ በመረጋገጡ ታምኖበት እርምጃ መወሰድ የተጀመረው እንቅስቃሴ “የረፈደ ቢሆንም የሚበረታታ ነው” በሚል የዞኑ ብልፅግና ፓርቲ አባላት በትናንትናው ዕለት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ መናገራቸው ይታወሳል።

አክለውም በዎላይታ ዞን ከብልጽግና ፓርቲም ሆነ ከመንግስት በበለጠ የሚፈራውና የመንግስት ሆነ የፓርቲውን ቅቡልነት እንዲያጣ ባደረገው እንዲሁም በአከባቢው መንግስታዊ አደረጃጀትን ተክቶ በተዘረጋውና የህዝብ አንድነትን እየተፈታተነ በሚገኘው በዚሁ አደገኛ የግለሰቦች አደረጃጀት ለማረም የፈደራል እና የክልል መንግስት ጋር በመተባበር የጀመረው መልካም ጅምር ህዝባዊ ድጋፍ ያለው በመሆኑ የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነም አባላቱ አሳስበው ነበር።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቤታሎ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *