ለመንግሥት ስራተኞች ደመወዝ ክፍያ ከክልሉ የሚበጀት በቂ ቢሆንም ከአሰራር ውጪ እየከፈሉ ሰራተኛው እንዲራብና እንዲማረር በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ከዞን፣ ከወረዳ እና ከከተማ አስተዳደር ለተወጣጡ ባለሙያዎች ላለፉት 13 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል።

ቢሮው ከተለያዩ አካባቢዎች ለተወጣጡ 220 የፋይናንስ ባለሙያዎች በበጀት፣ ክፍያ፣ ሂሳብ፣ ግዥ፣ ንብረትና የኦዲት አስተዳደር ስልጠና ሰጥቷል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ስልጠናው በፋይናንስ ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ተፈሪ በማጠቃለያቸው በክልሉ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ዜጋ መረባረብ እንደሚገባዉ አሳስበዋል።

አቶ ተፈሪ አያይዘውም ወደታች የሚወርደው ሀብት የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ መክፈል የሚያስችል ቢሆንም ከአሰራር ውጪ ‘በፐርሰንት‘ እየከፈሉ ሰራተኛው እንዲራብና በክልሉ ላይም እንዲማረር በሚያደርጉ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።

አቶ ተፈሪ ከአሰራር ውጪ የሚወርደውን ሀብት በማባከን ላልተገባ ወጪ በማዋል ዜጎች እንዲማረሩና የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላትን ሰልጣኙ ማጋለጥ እንደሚገባው አሳስበው ክልሉ በበጀት ዓመቱ 19 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ አቅዶ እስካሁን 11 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የገለፁት ኃላፊው በቅርቡ “የገቢ ማሰባሰብና የሀብት አስተዳደር ዘመቻ” በሚል ንቅናቄ እንደሚያካሂድም አስረድተዋል።

የመንግስት ሰራተኛን ደመወዝ በመከልከል የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሚወስድ በመግለፅ ሀብትን በተገቢው መንገድ መሰብሰብ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው ወጪዎችን መቀነስ እንደሚገባና በተለይ ከባህል አልባሳት ግዥ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረግ ደንብ እንደሚኖርም ገልፀዋል። #Wolaita #Times

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *