ክልሉ ደብዳቤዎችን በአድራሻዋ እየተቀበለና እየተላከለት የከተማውን ስም በግልጽ እንደሌሎቹ አሳትሞ የህግ አካል አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን ለመፃፍ እንኳን እንዴት አቃተው🔐❓ለመሆኑ የክልሉ አስተዳደር ዋና ፅህፈት ቤት ሕንፃ ለምን አልጀመረም❓

የቀድሞ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፈርሶ በአዲስ ከተዋቀሩት መካከል የፓለቲካና የአስተዳደር ማዕከሉን በዎላይታ ሶዶ ከተማ በማድረግ የተዋቀረው “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ከሌሎቹ የሚለየው በተለያዩ መንገዶች ስለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ እየፈጠረ እንደሆነ ባደረግነው የዳሰሳ ምልከታ ታዝበናል።

ለምሳሌ ቁልፍ የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ጨምሮ የክልሉ የፓለቲካና የአስተዳደር መዋቅር ማዕከል በመሆን ይፋ ተደርጎ አገልግሎት እየተሰጠበት የሚገኘው ዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ የተወሰኑ መዋቅሮች ቢሯቸውን ለመገንባት ከዞኑ መሬት በመውሰድ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም ቀሪዎቹና ዋናዎቹ በክራይና ቀድሞ በዞኑ በጀት በተገነቡ ቤቶች ላይ በመሆን ይሄንን ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ አለመሆኑ ተገቢ አይደለም የሚል ድምፅ ይደመጣል።

ሌላው የክልሉ ህገመንግስት እስካሁን በይፋ ስለ ክልሉ አስተዳደርና የፓለቲካ ማዕከል በግልጽ እንደሌሎቹ አሳትሞ የህግ አካል አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ለመፃፍ እንኳን አለመቻሉ በበርካቶች ዘንድ ጥርጣሬ እየፈጠረ ስለመሆኑም ለማወቅ ችለናል።

የተለያዩ የታሪክ ሰነዶች እንደሚያረጋግጡት የዎላይታ ህዝብ ከ7 ዓመታት እልህ አስጨራሽ የኢትዮ – ዎላይታ ጦርነት መጠናቀቅ በኃል (1887 ዓ/ም) ዎላይታ ከነበረው ገናና ታሪክና ሁሉ አቀፍ ከፍታ አንጻር መቀመጫውን ዎላይታ ያደረገና በቀጥታ ለፌዴራሉ መንግሥት ተጠሪ የሆነ አስተዳደራዊ መዋቅር (ስያሜው ክልል፣ ክ/ሀገር፣ ጠቅላይ ግዛት ወይም ሌላ ይሁን) ሊሰጠው ይገባ ነበር።

በአጼ ኃ/ሥላሴ ዘመኔ መንግሥት ዎላይታ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ሥር በአውራጃ ደረጃ ተዋቅሮ ይርጋለምና አዋሳ ለዘመናት የመመላለስ የመንከራተት ግዴታ ነበረበት።

ደጃዝማች ወ/ሰማያት ገ/ወልድ ወደ ዎላይታ ሲመጡ ከንጉሡ የተሰጣቸውን የሥራ አመራር ሲገልጹ “_ _ _ ዎላይታ አውራጃ ይሁን እንጂ በጠቅላይ ግዛት ደረጃ የምንመለከተውና የምንከታተለው አከባቢ በመሆኑ የልማት ሥራ ሰርተህ የሕዝቡን ልብ ወደ ፌዴራል መንግሥት መልስልን- – – ” የሚል ይሁን እንጂ ጠቅላይ ግዛት ስለሚገባው ብለው የጠቅላይ ግዛት ደረጃ ለመስጠት አልፈቀዱም ነበር።

በደርግ ዘመነም መንግሥት ዎላይታ ይባስ ጭቆና በርትቶበት ዎላይታ የሚል መጠሪያ ተከልክሎ የመዋቅር ጭቆና ቀንበር አርፎበት በወረዳ ደረጃ ተከፋፍሎ ገና ወደ ተመሰረተች አዲስ ከተማ ለመጓዝ ተገዶ እንደ ዋዱ (WADU) አይነት ግዘፍ ልማት ድርጅት “ለአንድ ወረዳ/ አውራጃ/ የዚህን ያህል መዋዕለ ነዋይ ምን ያደርጋል?” በሚል የዎላይታን ሕዝብ በብዙ መልኩ የጎዳ ውሳኔ ወስኖ በዓለም ባንክና በአሜሪካን መንግሥት ይደገፍ የነበረውን ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት በትኗል።

የኢህአዴግ መንግሥት በትግል ወቅት (ጫካ) በነበረው የአስተዳደራዊ መዋቅር ዕቅድ ዎላይታን ክልል 9 በሚል ለፌዴራል መንግስት ቀጥታ ተጠሪ እንዲሆን የያዘውን ዕቅድ በመተው መቀመጫውን በምንም መስፈርት ክልሉን በማያማክለው አዋሳ ከተማ ኦሮሚያ ክልል አፍንጫ ሥር አድርጎ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ሥር ሲያደራጅ የዞን መዋቅሩ በነበረበት እንዲቀጥል ከደርግ እኩል በግፍ እንዲደራጅ ቢያደርግም በ1992 ዓ/ም የዎላይታ ሕዝብ በከፈለው መስዋዕትነትና ብርቱ ትግል ቢያንስ በዞን መዋቅር ደረጃ ለማዋቀር ችሏል።

ዎላይታ በኢትዮጵያ ታሪክ ለፌዴራሉ መንግሥት በቀጥታ ተጠሪ የሆነ መዋቅር መቀመጫ መሆን የቻለችው ጣሊያን ሀገራችንን በወረረበት ወቅት የሀገሪቱን ዋና ከተማ ጂማ ለማድረግና የደቡብ ኢትዮጵያ አስተዳደራዊ መዋቅር መቀመጫ ዋና ከተማ ዎላይታ ሶዶ ላይ እንዲሆን መርጦ በቀጥታ ጂማ ላለው አስተዳደር ተጠሪ ሆኖ እንዲዋቀር አድርጎ በነበር ወቅት ብቻ ነው እንደሆነ ከታሪክ አዋቂ ሰዎች ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል።

ከዚያ ቀጥሎ ከ6 ዓመታት በፊት በሀገሪቱ በተፈጠረው የለውጥ ሂደት ከኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ሲሸጋገር በዎላይታ ሕዝብ ላይ ለዘመናት በተደጋጋሚ በተለያዩ ቦታዎች ይደርሱበት የነበሩ በርካታ በደሎች ጫፍ በመውጣታቸውና የቀድሞ ደቡብ ክልል መፍረስ ሲጀምር ዎላይታዊያን ከዚህ በኃላ “የራሳችንን ቤት እንገነባለን” በማለት ቆርጠው ተነስተው አላማው እውን እንዲሆን በርካታ ትግሎችን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ዘርፈ ብዙ ትግል በማድረግ የህይወት መስዋዕትነት፣ የአካል ጉዳት፣ እስር፣ ስደት፣ ከእንጀራ መፈናቀል፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቶችን ማስተናገድ እንዲሁም በሕግ አግባብ የቀረበው የዎብክመ ምስረታ ጥያቄ በቀድሞ የደቡብ ክልል መንግሥት ተከልክሎ ይግባኝ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ቢቀርብም ከሕግ አግባብ ውጭ ታፍኖ ተከልክለው ጉዳዩ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አማካይነት ወደ ፍርድቤት ተመርቶ እስካሁን ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል።

ከዚያ ሁሉ መስዋዕትነትና የትግል ጉዞ በኃላ የዎላይታ ዞን ም/ቤት የዎላይታ ክልል ጥያቄን በመሻር ከሌሎች አጎራባች ሕዝቦች ጋር በጋራ እንደራጃለን የሚል ውሳኔ ወስነው የህዝብ ጥያቄን ለዓመታት የነፈጉ የቀድሞ ደቡብ ክልል ም/ቤትና የፌዴሬሽን ም/ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ በማድረግ ነጭ እርግብ “በማሸነፏ” አዲሱ ክልል እውን መሆኑ ይታወሳል።

ሆኖም ግን “ክልሉ ከተመሰረተ ማግስት ጀምሮ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚጻፉ ህጋዊ ደብዳቤዎች ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ብለው ከሥር ዎላይታ ሶዶ የሚሉ ደብዳቤዎች በከተማዋ ስም አድራሻ እየተላከና እየደረሰ ባለበት የክልሉ ህገመንግስት ይሄንን እውነታ ተቀብሎ በደማቁ ፅፎ ለምን ለማሳተም አቃተው?” ቁልፍ የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ጨምሮ የክልሉ የፓለቲካና የአስተዳደር መዋቅር ማዕከል በመሆን ይፋ ተደርጎ አገልግሎት እየተሰጠበት በሚገኘው ከተማ ላይ የተወሰኑ መዋቅሮች ቢሯቸውን ለመገንባት ከዞኑ መሬት በመውሰድ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም ቀሪዎቹና ዋናዎቹ በክራይና ቀድሞ በዞኑ በጀት በተገነቡ ቤቶች ላይ በመሆን ለምን ዝምታ መረጡ?” የሚሉ ድምፆችም ከየአቅጣጫው ከፍ ብለው ይደመጣሉ።

ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ባለፈው ይፋ ባደረገው ምርመራ ዘገባችን “የአዲሱ ክልል ከህዝብ ፍትሃዊና ዕኩል ተጠቃሚነት አንፃር ምሁራንና የአከባቢው ነዋሪዎች ምን ይላሉ?” በሚለው አንድ የክልሉን ፓለቲካ በቅርበት የሚከታተል ምሁር ስንጠይቅ “ፍትሀዊ እና ተመጣጣኝ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ዉክልና ባለማግኘቱ አንኳር በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማስገኘት እንዲሁም የልማት ፍትሃዊነት ለማስጠበቅ ግልፅ እና አሳታፍ የህግ ሥርዓት ተዘርግቶ እንድመራ መግባባት ተፈጥሮ መስራት ሲገባ በአሁኑ ወቅት ከዚያ እውነታ በተቃራኒው ተጨባጭ እንቅስቃሴ መኖሩን መጠቆሙ ይታወሳል።

የፍትሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎች በሚነሱበት ወቅት አንዱን የህብረሰብ ክፍል አለአግባብ በመጥቀም ሌላውን አለአግባብ የሚጎዳበት አደገኛ ሁኔታ ስለሚፈጥር በክልሉ ከፍተኛ ህዝብ ቁጥር ያለው፣ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ፣ ከፍተኛ የተማረ ህብረተሰብ ክፍል ያለበት እንዲሁም ከፍተኛ የንግድና እንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያለበት፣ ለሀገራዊ ፕሮጀክት ድጋፎችና ጥሪ በሁሉም ዘርፍ ከሚገባው በላይ ሲያበረክትና እያበረከተ የሚገኘውን ህዝብ ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ ሁሉንም ህዝቦች በቅንነትና በታማንኝነት በህጋዊነት የሚገባቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ማገልገል የነበረባቸዉ በተቃራኒው ናቸውና ህዝቡ በፖለቲካ ሥልጣን ድልድልና በሀብት ክፍፍልም በተለይም የክልሉ ምክር ቤት በሚያውጃቸው ሀብቶች አስተዳደር ላይም ኢፍትሐዊ አሰራር ተደግሞ ለመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እንዳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባም ምሁሩ በማጠቃለያ ሀሳቡ ጥሪ አቅርበው ነበር። Wolaita Times

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *