የደቡብ ኢትዮጵያ ከልል የፖለቲካ እና የአመራር ብልሽት ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የፀጥታ ራስ ምታት የመሆን ስጋት አንገብጋቢ አዝማሚያዎች እንዳሉ ምሁራን አሳስበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ያሉበት የብዝሐ ብሔር፣ ባህል፣ ቋንቋ ታሪክ ያለው ክልል በመሆኑ ችግሮችን በጊዜው መቅረፍ ካልተቻለ እየተባባሰ እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡

ይህ ክልል የቀድሞ ደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልላዊ መንግሥት በአራት ቦታ ሲከፋል ከተመሠረቱ ክልሎች አንዱና ወደ 10 ሚሊዬን የሚጠጋ ሕዝብ ያለበትም ክልል ሲሆን እንደ ምሁራኖች ገለፃ ይህ ክልል ከመመስረቱ በፊት በአከባቢው በርካታ ፖለቲካዊ እና የአደረጃጀት ጥያቄዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሲነሱበት የነበረ ከልል ነው፡፡

ከአደረጃጀት ጥያቄዎቹ መካከል የዎላይታ ሕዝብ ሲጠይቅ የነበረው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ግንባር ቀደም ሲሆን ሌሎች በርካታ የብሔር ማንነት ጥያቄ፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ጥያቄዎች የነበሩበት ሲሆን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከነበሩት ነባር ችግሮችና ጥያቄዎች በተጨማሪ በአደረጃጀት ሂደቱ ላይ የነበሩ ጉልህ ስህተቶችና ክልሉ ከተደራጀም በኋላ እየተፈፀሙ ያሉ የመልካም አስተደዳር ጉድለቶች፣ የሥልጣን ላይ ብልግና፣ የሕግ የበላይነት መጥፋት፣ የክልሉ አስተዳደር ወሣነዎች መርህ የለሽ መሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋው ሙስና እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክልሉን ለመፍረስ አደጋ ከመጋረጣቸው በላይ አሁን ሀገሪቱ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በሌሎች ከልሎች እየገጠማት ከሚገኘው የፀጥታና የፖለቲካ ችግር ተጨማሪ ራስ ምታት ወደ መሆን እየደረሰ ይገኛል፡፡

እንደዚያም ሆኖ በደቡብ ኢትዮጵያ ከልል የሚገኘው አስጊ ችግር የፌዴራል መንግስት በቂ ትኩረት ያገኘ አይመስልም፡፡ በዚህም ምከንያት ክልሉ ሽኩቻ የበዛበት ሲሆን በአፋጣኝ ካልታረመ ለወደፊቱም ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል የሚሰጉ መሆናቸውን የአከባቢውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በንቃት የሚከታተሉ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና የገዥው ፓርቲ አባላት ሆኑ የመንግስት ሠራተኞች ይገልፃሉ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ችግሮች ዋናዎቹ ምንድን ናቸው; መነሻቸውስ ምንድንነው❓

  1. የክልሉ ማዕከል ከተሞችን በመወሰን ሂደት የተፈጠሩ ከፍተኛ ሽኩቻዎችና እነዚያ ሽኩቻዎች የፈጠሯቸው ተቃርኖዎች ሳይወገዱ በችኮላ ወደ ክልል ምስረታ መገባቱ፤
  2. የክልሉ ማዕከል ከተሞች መብዛትና የክልሉ ቢሮዎች ተበታትነው በመገኘታቸው በሕዝቡ፣ በክልሉ ሠራተኞች ያስከተለው እንግልትና ከፍተኛ የሆነ የበጀት ብክነት፤ ( የተዘዋዋሪ ችሎት ጉዳይ)
  3. የክልሉ መንግስት መቀመጫ ከተማ በውል ለይቶ ያለ ማስቀመጥና በክልሉ ህገ-መንገስትም ጭምር የሚታየው ብዥታ ( የክልሉ መንግሥት መቀመጫ በሆቴል ነው ወይስ ሶዶ; )
  4. በክልሉ ምላሹ ባላገኙ የአስተዳደር እና የማንነት ጥያቄዎች ምክንያት እየተፈፀሙ የሚገኙ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ( በቁጫ፣ በሻራ አከባቢ፣ በዛይሴ፣ በቦሮዳ ወዘተ እየተፈፀሙ ያሉ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስራት እና መፈናቀል)፤
  5. በክልሉ ሀብት የሚያስተዳድሩ ቢሮዎችን በመደልደል ሂደት የተፈጠሩ አድሏዊና ግልፅነት የጎደላቸው አሠራረሮች ጎልተው መታየታቸው፣
  6. በክልሉ በጉልህ እየታየ የሚገኘው የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍልና የአኮኖሚ ተጠቃሚነት ኢፍትሐዊነት፤
  7. የክልሉ አስተባባሪ አካላት ለሁለት በመሰንጠቅ ጎራ ተለይቶ መካረር መጀመሩ እና ይህም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ መዝለቁ፤
  8. ከፍተኛ የሆነ ሙስና እና የሕዝብ ሀብት ዝርፊያ ( እስከ ፌዴራል ባለሥልጣናት ተዋናይ እንደሆኖቡት የሚጠረጠረው ከጥቂት ዘራፊ ባለ ሀብቶች ጋር በመመሳጠር በፕሮጀክቶች፣ ከድንጋይ ከሰልና ከሌሎች ማዕዳናት፣ የእርሻ መሬትና የከተማ መሬት ምዝበራ፣ የሆቴል መስተንግዶዎች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ )

ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን በተመለከተ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጨባጭ መረጃዎች የደረሱት ሲሆን በእያንዳንዳቸው አንኳር ጉዳዮች የተለያዩ አካላትን በማናገር ጭምር የተገኙ መረጃዎችን ማስረጃዎችን በመንተራስ ትንታኔ የምናቀርብ ይሆናል፡፡ በተጠቀሱ ጉዳዮች ተጨማሪ ማስረጃናና መረጃ ያላቸው አካላት በውስጥ መስመሮች ልያገኙን ይችላሉ፡፡

ማሳሰቢያ፡- የዚህ ዝግጅት ዋና ዓላማ በክልሉ ያሉ ችግሮች ጫፍ ደርሰው በአከባቢው ቀወስ ከመከሰቱ በፊት የሚመለከተው አካል፣ በተለይም የፌዴራሉ መንግሥት የእርማት እርምጃ እንዲወስድና ሕዝቡም ችግሮቹ የሚከሰትባቸውን ሁኔታ ተገንዝቦ በአከባቢው የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ማሳውቅ ብቻ መሆኑን ለማስገንዘብ እንነወዳለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *