“የህዝቦች ዕኩልነትና አብሮነት የሚረጋገጠው ሁሉንም በአበርክቶቱ መጠን በማገልገል እንጂ በመርህ አልባ መደጋገፍና ኢ-ፍትሐዊ ውድድሮችን ተግባራዊ በማድረግ አይመጣም” ሲሉ ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ተከተል ላቤና ገልጸዋል።

በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የህግ መምህር እንዲሁም ጠበቃና የህግ አማካሪ ተከተል ላቤና በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ የሚገኘውን አስተዳደራዊ መርህና ኢፍትሃዊነት በተመለከተ “የሚበጀን የትብብር ውድድር እንጂ ፍትሃዊ ያልሆነ ውድድር አይደለም” በሚል ምልከታውን አካፍለዋል።

የህግ መምህሩ “ሌላውን ማህበረሰብ ወይንም አመራር በማሳነስ መተለቅ እንደማይቻል እስካሁን ካልገባን የትልቅነት ትርጉም ከቅልነት ትርጉም ጋር አልገባንም ማለት ነው” በማለት ተችተዋል።

“ከቤተ-እምነት እስከ ቤተ መንግስት ድረስ ለሚታስተዳድራቸው ህዝቦች የሚገባቸውን ፍትሐዊ ድርሻ መስጠትና በአተገባበሩ ግዴታ መጣል ይገባል፥ ምክንያቱም መብትና ግዴታ አይነጣጠሉም” ብለዋል።

“በህዝቦች መካከል ዕኩልነትን መሠረት ያደረገ አብሮነት የሚመጣው ሁሉንም በአበርክቶቱ መጠን መዳኘትና በማገልገል ሲጀመር እንጂ በመርህ አልባ መደጋገፍና ኢ-ፍትሐዊ ውድድሮችን በዳተኝነት በማረታታት አይደለም” በሚል ጠበቃው ኢፍትሐዊነትን አውግዘዋል።

“የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሀገርቷ ህገ መንግስትና ሌሎች ህጎች የሥልጣንና የበጀት ድልድል ቀመሮችና መርሆዎች መሠረት ከክልሉ ምስረታ በፊት ተዋዶና ተዋልዶ የሚኖሩ ወንድማማች ህዝቦችን ለተሻለ ሁለንትናዊ ብልፅግና በመዳረግ በመላ ሀገርቷ ፍትሐዊ መብቱንና ግዴታውን የሚወጣ ጠንካራ ክልል እንዲሆን ሚዛናዊ አስሀዳደር ማረጋገጥ ግድ ይላልም” ብለዋል።

የህግ መምህሩ በክልሉ እየተስተዋለ የሚገኘውን ሁኔታ ላይ “ከአመራር እስከ ህብረተሰቡ ድረስ በመርህ ላይ የተመሰረተ የትብብር ውድድር አካሄድ በመከተል በጋራ መተለቅን ያመጣል። በዚህ መርህ በተራ ተራ የፖለቲካ ሥልጣንን ሁሉም እንዲቀባበለው ማድረግ ይችላል። ነገር ግን የአስተዳደር ሥርዓቱና ፍልስፍናው ፍትሐዊ መሆኑን ሁላችንም የማረጋገጥ መብትም ግዴታ አለብን” በሚል የመፍትሔ አቅጣጫንም ጠቁመዋል።

“በአመራርና ከአመራር አጀንዳ ተቀባይ በማህበረሰብ አንቂዎች መካከል እየተስተዋለ ያለው ፍትሃዊ ያልሆነ ውድድር ወደ ማህበረሰቡ ዘልቆ ከገባ ፈተኝ የመሆን ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ብልፅግና እንደ ፓርቲ የውስጥ ድሲፒሊን ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበትና በህዝቦች መካከል ያለ አብሮነት ትላንትም ዛሬም ነገም ፀንቶ የሚቆይ ስለሆነ ጥንቃቄ ሊናደርግ ይገባል” በሚል ጠበቃና የህግ አማካሪ ተከተል ላቤና አሳስበዋል።

ባለፈው ሳምንት የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በምርመራ ዘገባው “የአዲሱ ክልል ከህዝብ ፍትሃዊና ዕኩል ተጠቃሚነት አንፃር ምሁራንና የአከባቢው ነዋሪዎች ምን ይላሉ?” በሚለው አንድ የክልሉን ፓለቲካ በቅርበት የሚከታተል ምሁር “ፍትሀዊ እና ተመጣጣኝ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ዉክልና ባለማግኘቱ አንኳር በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማስገኘት እንዲሁም የልማት ፍትሃዊነት ለማስጠበቅ ግልፅ እና አሳታፍ የህግ ሥርዓት ተዘርግቶ እንድመራ መግባባት ተፈጥሮ መስራት ሲገባ በአሁኑ ወቅት ከዚያ እውነታ በተቃራኒው ተጨባጭ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁሟል።

ህገመንግስት ያጎናፀፈውን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ህጎች በህገ-መንግስት ጭምር እንዲካተት በማድረግ አዋጆች፤ ደንቦች እና መመሪያዎች ተዘጋጅተዉ ወደ ተግባር መገባቱን በመግለፅ ለአብነት በክልሉ በብሄረሰቦች ም/ቤት አማካይነት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የበጄት ቀመር የማዘጋጀት፤ በሰራተኞች ምደባ እና ዝዉዉር ለሁሉም ዞኖች እኩል በማድረግ በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የተጀመረ በሌሎች ቢሮዎችና አሰራሮች የሚቀጥል ከሆነ በአከባቢው ኢፍትሐዊነት ሰፍኖ አደገኛ የመልካም አስተዳደርና የፓለቲካ አለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችልም ምሁሩ ስጋቱን ገልፀው ነበር።

የፍትሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎች በሚነሱበት ወቅት አንዱን የህብረሰብ ክፍል አለአግባብ በመጥቀም ሌላውን አለአግባብ የሚጎዳበት አደገኛ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት እንዲሁም የአስተዳደር ፖለቲካ የመምራት ኃላፊነት ተቀብለው እየሰሩ የሚገኙ አካላት የፍሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎችን በተገቢው ተረድተው “ለራስ በልዩነት” ከሚለው አስተሳሰብና ድርጊት ተቆጥበው በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም ህብረተሰቡ ክፍሎች የሚገባቸውን ጥቅምና ክብር መስራት እንደሚገባ አክለው መጠቆሙ ይታወሳል።

በክልሉ ከፍተኛ ህዝብ ቁጥር ያለው፣ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ፣ ከፍተኛ የተማረ ህብረተሰብ ክፍል ያለበት እንዲሁም ከፍተኛ የንግድና እንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያለበት፣ ለሀገራዊ ፕሮጀክት ድጋፎችና ጥሪ በሁሉም ዘርፍ ከሚገባው በላይ ሲያበረክትና እያበረከተ የሚገኘውን ህዝብ ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ ሁሉንም ህዝቦች በቅንነትና በታማንኝነት በህጋዊነት የሚገባቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ማገልገል የነበረባቸዉ አንዳንድ ተቋማት በተቃራኒው ናቸውና ህዝቡ በፖለቲካ ሥልጣን ድልድልና በሀብት ክፍፍልም በተለይም የክልሉ ምክር ቤት በሚያውጃቸው ሀብቶች አስተዳደር ላይም ኢፍትሐዊ አሰራር ተደግሞ ለመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እንዳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባም ምሁሩ በማጠቃለያ ሀሳቡ ጥሪ ማቅረቡን መዘገባችን አይዘነጋም።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *