በጎፋ ዞን የ3 ወር ውዝፍ ደመወዝ የጠየቁ እና የWT Mediaን ዘገባ ያጋሩ መምህራን በጅምላ ታስሯል
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን የኦይዳ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞችና መምህራን የሦስት ወራት ውዝፍ ደመወዛቸውን በመጠየቃቸው እና WT Media ስለጉዳዩ የዘገበውን ዘገባ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው በማጋራታቸው፣ በጅምላ እስር ላይ መሆናቸውን የመምህራን ተወካዮች በዛሬው ዕለት ለWT WT Media አስታውቋል።
የጭቁኖች ድምፅ የሆነው WT Media (ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ) ከቀናት በፊት በዘገበው መሠረት፣ በኦይዳ ወረዳ የ2 ወራት የ2016 ዓ.ም. እና የ1 ወር የ2017 ዓ.ም. ውዝፍ ደመወዝ ጥያቄ ሦስተኛ ዓመቱን መያዙን ተከትሎ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩን ይፋ አድርጎ ነበር።
የመንግሥት ሠራተኞቹ ያቀረቡት ቅሬታ የጠቅላላ 235% የሚሆን ውዝፍ ደመወዛቸውን “ማን እንደበላ፣ ወዴት እንደገባ ወይም ምን እንደዋጠው የሚያስረዳ አካል” ጭምር እንዳጡ ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ሠራተኞቹ ለሦስት ዓመታት ያህል በተደጋጋሚ የወረዳውን መንግሥት ቢጠይቁም፣ “እንከፍላለን” የሚል “ሰማይ ላይ ላም አለ” ዓይነት ተስፋ ብቻ ተሰጥቷቸው መቆየቱን ገልጸዋል።
በወቅቱ የኦይዳ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጥያቄያቸው እንዲመለስ፣ ጉዳዩ “ይህ የደመወዛችን ጥያቄ ይመለከተኛል የምል የሕዝብ ኃላፊነት የሚሰማው እና ሹመቱ ከክርስቶስ የሆነ ለዜጋው የሚያስብ ካለ” በማለት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ዛሬ በደረሰን አስቸኳይ መረጃ መሠረት፣ ውዝፍ ደመወዝ የጠየቁ እና WT Media ስለጉዳዩ የሠራውን ዘገባ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ያጋሩ ብዙ መምህራን ከያሉበት እየተፈለጉ በፀጥታ አካላት እስር ላይ ይገኛሉ።
የመምህራን ተወካዮች ለWT Media ሲናገሩ፣ “WT Media ባለፈው ቀን በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ ስለ ውዝፍ ደሞዝ ችግር ድምፅ ሆኖ መዘገቡን ከልብ እናመሰግናለን፣ የጭቁኖች ድምፅ ስለሆናችሁ።
ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ዘገባውን ያጋሩ መምህራን ከያሉበት እየተፈለጉ እስር ላይ ናቸውና እንደተለመደው ድምፅ ሁኑልን” በማለት አስቸኳይ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይህ የመምህራን እስር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናት መልካም አስተዳደርን የመስጠት ኃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ፣ የዜጎችን የመጠየቅና የመናገር መብት ለማፈን በኃይል እርምጃ መውሰድ መርጠዋል የሚለውን አሳሳቢ ሁኔታ ያጠናክራል።
WT Media የጭቁኖች ድምፅ እንደመሆኑ መጠን፣ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ፣ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የፍትሕ መጓደል ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ ያደርጋል።