በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በመሬት ናዳ ምክንያት ለተጎዱና ለሞቱ ቤተሰቦቻቸው ከበርካቶች የተሰበሰበውን የእርዳታ ገንዘብ “ዘረፋውን አጋለጣችሁ” በሚል ከ20 በላይ ወጣቶችና በፍትሕ አካላት ላይ የሚፈጸመው የአፈሳና የእስራት ዘመቻ ተባብሶ መቀጠሉ ተገልጿል።
በጎፋ ዞን የደረሰውን የኬንቾ ሻቻ አደጋ ተገን በማድረግ የተፈጸመውን የግማሽ ቢሊዮን ብር ምዝበራ በተመለከተ WT Media ያወጣውን ተከታታይ ዘገባ ተከትሎ፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳግማዊ አየለ መረጃውን አውጥታችኋል ያላቸውን ወጣቶችና የፍትሕ አካላት እያፈሱ የማሰር እርምጃ መጀመራቸውን ከስፍራው የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
“የአደጋ ሥጋት አካውንቱ ኦዲት ይደረግ” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ ሲጠይቁ የነበሩ ወጣቶች የአስተዳዳሪው ቀዳሚ ኢላማ ሆነዋል። ላለፉት ሁለት ቀናት ብቻ፦
ከ20 በላይ ወጣቶች በሳውላ ከተማና አካባቢው ታፍሰው ታስረዋል።
ሁለት የማረሚያ ቤት ፖሊሶች የታሰሩ ሲሆን፣ አንድ የሳውላ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ ደግሞ “የአስተዳዳሪውን ትዕዛዝ አላከበርክም” በሚል ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።
አስተዳዳሪው በራሳቸው ላይ እየወጣ ያለውን መረጃ ለማፈን የኃይል እርምጃቸውን ወደ ጎረቤት ከተሞችም አስፋፍተዋል።
በተጨማሪም በዎላይታ ሶዶ፣ በአርባምንጭና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለማሰር ፖሊሶች መጥሪያ ይዘው መሰማራታቸውን ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያረጋግጣል።
ይህ እርምጃ አስተዳዳሪው በወንጀሉ ውስጥ እጃቸው መኖሩን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ተደርጎ ተወስዷል።
ቁልፍ ተጠርጣሪው መሐመድ ኑሩ ሑሴን፣ “ወንጀሉን ከአስተዳዳሪው ጋር በጋራ ነው የሰራነው” በሚል ቃሉን ለፖሊስና ለዓቃቤ ሕግ መስጠቱን ተከትሎ፣ አቶ ዳግማዊ አየለ ይህን ምስክርነት ለማጥፋትና መረጃ ያቀበሉ ሰዎችን ለማሸበር የጥፋት እርምጃ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።
በተለይም በሳውላ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ምስክሮች ሕይወት አሁንም በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
WT Media የሕዝብን ሀብት የበሉና የሟቾችን ደም የዘነጉ ባለሥልጣናት ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርገውን ዘገባ አጠናክሮ ይቀጥላል።
ለክልሉና ለፌደራል መንግሥት፦ በፍትሕ አካላትና በንጹሐን ወጣቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገ-ወጥ እስራት በአስቸኳይ እንዲቆም ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል።
በጎፋ ዞን እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የታሳሪዎችን ሁኔታ እንዲከታተሉ ጥሪ እናቀርባለን።
WT Media በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ በመረጃና በማስረጃ በማስደገፍ በቁርጠኝነት እየዘገበ የቆየ ሲሆን፤ አሁንም አደጋው የደረሰባቸው ወገኖች ፍትሕ እስኪያገኙ እና በሕገ-ወጥ ድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በሙሉ ለሕግ ቀርበው ተጠያቂነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ ድምፅ መሆኑን አጠናክሮ ይቀጥላል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media