GridArt_20260520_175028966

​በታዋቂው የባህር ዳር ከተማና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አለልኝ አዘነ የግድያ መዝገብ ላይ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዎላይታ ምድብ ችሎት ነገ ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይዟል።

WT Media ጉዳዩን ከመጀመሪያው ጀምሮ በቅርበት ሲከታተልና ተከታታይ የዜና ሽፋኖችን ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከነገው ወሳኝ ችሎት በፊት ከተለያዩ የቅርብ ምንጮች የተገኙ መረጃዎች በጉዳዩ ዙሪያ አዳዲስ ጥርጣሬዎችንና ስጋቶችን አስነስተዋል።
​
​ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የቅርብ ወገኖች ለ WT Media እንደገለጹት፣ በግድያ ወንጀሉ ጥፋተኛ የተባለችው የአደይ ጌታቸው ወገኖች የይግባኝ ሂደቱን ተጠቅመው በነፃ ለመሰናበት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

​የሟች አለልኝ አዘነ ወላጆች፣ ልጃቸው ከመሞቱ በፊት በባለቤቱ እጅ የነበሩትን ሁለት ቤቶችና የተለያዩ ንብረቶች ለማስመለስ የፍትሐብሔር ክስ መስርተው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ንብረቱን ላለመመለስና ሂደቱን ለማስተጓጎል ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ተገልጿል።

በግድያ ወንጀሉ ጥፋተኛ የተባለችው የአደይ ጌታቸው እናት የጎፋ ተወላጅ መሆናቸውን የጠቀሱት ቤተሰቦቹ፣ የወቅቱ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ በጋለ ጎፋ የቅርብ ዘመድ መሆናቸውን በስጋትነት አንስተው ነበር።

​መዝገቡ ወደ ዎላይታ እንዲዛወር የተደረገው በፕሬዝዳንቱ ትእዛዝ በተሰየሙ ዳኞች አማካኝነት እንደሆነና ይህም “በገንዘብና በትውውቅ” ፍትህን የማጣመም ሂደት መሆኑን ቤተሰቡ በምሬት ገልጸዋል።

​የህግ ባለሙያዎችን በማማከር እንደተረዱት፣ በቅርብ ባለ ችሎት ጉዳዩን ማየት ሲቻል፣ ሆን ተብሎ ግራ ቀኙ ሳይመክሩበት በሁለት ገጽ ደብዳቤ ብቻ መዛወሩ አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው “ስልጣንን መከታ በማድረግ ፍትሕን ለማዛባት ከሚደረግ ጥረት” ጋር የተያያዘ ነው የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬ አስነስቷል።

​በወንጀል ህጉ መሰረት አንድ ሰው የትዳር አጋሩን ህይወት ካጠፋ ከንብረት ውርስ ውድቅ እንደሚሆንና እንደማይመለከተው በግልፅ ቢደነገግም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይግባኝ ሰሚው አካል “ነገሮችን በማድበስበስ ጥፋተኞችን በነፃ ለመልቀቅ” እያሴረ ነው የሚል ስጋት በስፋት እየቀረበ ነው።

​ቤተሰቦቹ ቀደም ሲል ሚያዝያ 13 ቀን በነበረው ቀጠሮ መዝገብ ጠፍቷል በሚልና ዳኞች አልተስማሙም በሚሉ ምክንያቶች ለአንድ ወር መራዘሙ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና እና የኢኮኖሚ ጫና እንደፈጠረባቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

WT Media ከተጎጂው ቤተሰብ ጎን በመቆም ፍትሕ እስኪረጋገጥ ድረስ በየደረጃው የነበሩትን እንግልቶችና የተጽዕኖ ስጋቶች በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ነገ ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚሰጠው ውሳኔ፣ የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ያለምንም ዝምድና፣ ጥቅምና የባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ፍትሕን በተግባር የሚያሳይበት መሆን እንዳለበት የተጫዋቹ ወዳጆችና ቤተሰቦች በአፅንኦት ያሳስባሉ።

​WT Media የነገውን የችሎት ውሳኔ በቀጥታና በቅርበት መከታተሉን አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል።